Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በመንፈስ የኩሽ ዘር ነኝ ክፍል ፩

በያሬድ ነጋሽ

አንድ ሰው በትውልድ፣ በዘር ግንድ፣ በሃይማኖት፣ በቀለም፣ ወዘተ ከአንደኛው ወገን ብያኔ ውስጥ ይሆንና ሆኖም ከተማረከባቸው በጎ ሐሳቦች በመነሳት ከወገኑ ተለይቶ በመንፈስ የትም ሊወለድ፣ ማንንም ሊመስል፣ ከወዳኛው ሃይማኖት ጉባዔ ሊሳተፍ የሚያግደው ነገር የለም፡፡ እኔም በመንፈስ የኩሽ ዘር ነኝ፡፡

ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ኢየሱስና  ከጥንታዊ የኩሽ ምድር አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅና ግሪኮ-ሮማን አፈ ታሪክ ጋር ተያይዞ በድንግልና የሚወለዱ፣ የሚሞቱበትና በኋላም ወደ ሕይወት የሚመለሱ አማልክት ይገኛሉ፡፡

‹‹‘ከሙታን የመነሳት ትውፊት የጀመረው በካም እናት አድባር አቴቴ ከአሥር ሺሕ ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ነው’ ይላል፡፡ ልጇ ይገዳደላሉ፡፡ ኦራ ወይም ሳቦ የተባለው ልጇ በወንድሙ በሴት ወይም ጉና ተገደለ፡፡ አቴቴ ከእህቷ ከነፍትየስ ጋር ሆና ኦራን ወደ ትንሳዔ ልደት ይቀሰቅሱታል›› (ሐሰተኛው በእምነት ስም፣ በዓለማየሁ ገላጋይ፣ ገጽ 293)፡፡

‹‹ጥንታዊ የሜሶጶጣሚያ አምላክ ዱሙዚድ ወይም በሱመርያን ዱማዚድ ወይም በሮማውያን ሲፓድ፣ ዱሙዚ፣ ታሞ እንዲሁ ሞቶ ተመልሶ እንደተነሳ፣ የግሪክ ዕፀዋት አምላክ አቲስ ‘በክረምት ወራት የሚሞቱት አዝርዕት [በመፀው] ወቅት እንደገና ይነሳሉ’ ከሚለው በመመሥረት ሞቶ የተነሳ አምላክ ይሉታል›› (የሚሞቱና የሚነሱ አማልክት ታሪክ፣ በድሪክ ቤርስ)

በጥቁር አሜሪካውያን ላይ አትኩሮቱን ያደረገው ኢቦኒ መጽሔት በመጋቢት 1969 ለንባብ ባበቃው ዕትም በድንግልና ተወልዶ፣ ሞቶ ስለተነሳው የመጽሐፍ ቅዱሱ ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ዕሳቤን ይዞ ብቅ አለ፣ ‹‹እውነተኛውን ጥቁር ኢየሱስ ፍለጋ›› በሚል ኢየሱስን በጥቁር ሰው አምሳል አስጊጦ የሽፋኑን ገጹ አደረገ፡፡ ይህ ክስተት በርካቶችን አስቆጣ፡፡ የቁጣው መጠንም በጥቁር ማኅበረሰብ ውስጥ እጅግ አይሎ በመገኘቱ በርካቶች አባልነታቸውን በመሰረዝ ድርጅቱ እንዲዘጋ ከማድረግ አንስቶ የመጽሔቱ ባለንብረቶችን ለመጉዳት እስከ ማስፈራራት፣ ‹‹እውነተኛው ኢየሱስ›› ብለው የሚጠሩትን ነጩን ምስል ለሕትመት ድርጅቱ መላክና መፈክር በሚመስል መልኩ ይዘው እስከመታየት ደረሱ፡፡ ይህንን የጥቁር ሕዝብ ምላሽ የተመለከቱት አንዳንዶች “Stockholm Syndrome” (አጥቂህን ወደማፍቀር የሚወስድ የሥነ ልቦና እክል) ብለው የወሰዱት አልጠፉም፡፡

ሐሳቡ ግን ወደ ጥንተ ታሪካችን እንድንመለስና በኢትዮጵያ ‹‹እኔ ጥቁሩ ኢየሱስ ነኝ›› ብሎ የተነሳውን ሰው እንድንመለከት ያስገድደናል፡፡ ‹‹ከጥቁሯ ድንግል ማርያም (መርዓተ ወንጌል) የተወለድኩ፣ የሞትኩ፣ የተነሳሁ ያረግሁ ጥቁሩ ኢየሱስ እኔ ነኝ በማለት ብዙ ተከታይ ያፈራውን ሰው አፄ ዘድንግል አስጠርተው ቢጠይቁት ሳይፈራ እኔ ክርስቶስ ነኝ አለ፡፡ …ንጉሡ ጭንቅላቱን አስቆረጡት፡፡ ተከታዩቹ ጌታችን ከሙታን ተነስቷል የሚል ምስክርነት ሰጡ›› (ሐተኛው በእውነት ስም ገጽ 291-292)

በመጀመሪያ ኢቦኒ መጽሔት ይሁን በኢትዮጵያ የተነሳውም መሲህ በዚህ መልኩ መምጣታቸው ከምን ተነስቶ ነው? የአጥቂዎቻቸውስ ምላሽ ከምን የመነጨ ነው? የሚለው ጥያቄ መነሳት ይገባዋል፡፡ ከኢቦኒ ጋር ስለተገናኘው ጉዳይ የሐሳቡ መነሻ ነጮቹ በክርስትና ሃይማኖት ከለላ በጥቁሩ ማኅበረሰብ ላይ የግፍ ግፍ ከማድረሳቸው በተጨማሪ ወላፈኑ ዛሬ ድረስ ደርሶ በተፅዕኖ ሥር በመውደቃችን፣ ከተፅዕኖ ማምለጫው ስልት ወደራስ መመልከት ብቻ አማራጭ የሌለው መፍትሔ እንደሆነ በማመናቸው ነበር።

ክርስትናን ያለአግባብ ተጠቅመውበታል ለሚለው በተጨባጭ ማመሳከር የፈለገ ሰው፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለጥቁሩ ማኅበረሰብ ካደሉ በኋላ ክርስትናን ያለአግባብ ለመጠቀማቸው ማስረጃ በሚሆን መልኩ ‹‹ባሪያዎች ሆይ፣ ለክርስቶስ እንደምትታዘዙ፣ በምድር ጌቶቻችሁ ለሆኑት በአክብሮትና በፍርኃት፣ በልብ ቅንነትም ታዘዙ፣ ለታይታና ከእነርሱ ሙገሳን ለማግኘት ሳይሆን እንደ ክርስቶስ ባሪያዎች የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም ታዘዟቸው›› (ኤፌሶን) የሚለውን አብዝተው በመጥቀስ ለራሳቸው ግን የሥርዓት ማሳለጫ ስልት እንዲሆን የተጠቀሙት ቅዱስ መጽሐፉን ሳይሆን በDr. Reverend Charles Colcock Jones እንደተጻፈው How to Make a Negro Christian ዓይነት መጻሕፍትን ማጣቀሻ በማድረግ ነበር፡፡ ይህንንም በመጽሐፉ ዙሪያ ጥልቅ ትንተና በመሥራት አስተያየት የሰጡት Kamau Makesi-Tehuti መስክረዋል።

ኬንያ ቶክ በኢቦኒ መጽሔት የተነሳውን ሐሳብ በመመርኮዝ የበርካታ ጥቁር አፍሪካውያን ወጣቶች ጥያቄን አንግቦ አንድ ዘገባ ሠርቶ ነበር፡፡ ‹‹ነጭ የባሪያ ጌቶችና የአፍሪካ ቅኝ ገዥዎች ጥቁሮችን ወደ ክርስትና ለመለወጥ አስፈላጊ ሆኖ ያገኙበት ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ምላሹን ለመስጠት ሲሞክር ‹‹እንደ ነጮቹ አባባል ከሆነ ጥቁሮች የክርስትና ሃይማኖት አልተቀበልንም ነበር፡፡ ይኼም ማለት ጥቁሮች በእውነት ነፍሳቸው ከፈጣሪ ያልተገናኘች እንደሆነ ተገነዘቡ፡፡ ‘በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለ ጥቁር ሰው ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባል ተብሎ ማሰብ ውሻ ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባል እንደማለት ያህል አስቂኝ ነው’ ብለው ዘበቱ፡፡ ስለዚህ ነጮች ነፍሳችንን በማዳን በኋለኛው የሰማይ ቤት ሕይወት ከእነሱ ጋር መንግሥተ ሰማያትን እንድንካፈል ፈለጉ፡፡ ይኼ ግን ‹‹ሰሙ›› ነው። 

ነገር ግን ወርቁን ስንመለከት የነጮች ባሪያ ጌቶችና ቅኝ ገዥዎች የክርስትናን ሃይማኖት ሲያስተምሩ የጥቁር ሕዝቦችን ነፍስ ለመታደግ አስበው እንዳልሆነ በቀላሉ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። እውነታው መጽሐፍ ቅዱስን የአፍሪካውያንን አዕምሮ ለማጠብ የተጠቀሙበትና አስተምሮቱም በነጭ አማልክት ብቻ እንዲያምኑ የሚያስገድድ (ነጭ እግዚአብሔር፣ ነጭ መሢሕ፣ ነጫጭ መላዕክትና ነጮች ነቢያት) ሲሆን ይህ የሆነበት ምክንያት የነጭ መለኮት ታሪክ በአፍሪካውያን ባሪያዎች አዕምሮ ውስጥ እንዲሰርጽ በማድረግ  የበላይነታቸውን ለማሳየት ሆን ብለው ያደረጉት ነበር።

የነጩ የእግዚአብሔር ልጅ ምስልን በነጭ ሲወክሉ የእግዚአብሔር ልጅ ነጭ ከሆነ እግዚአብሔር (አባቱ) እንዲሁ ነጭ መሆን አለበት የሚል ዕሳቤን እንድንገነዘብ ያደርገናል፡፡ እንደውም አውሮፓውያን የነጩን ኢየሱስን ወደ ጥቁር ሰዎች አዕምሮ ውስጥ ማስገባት መቻላቸው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከተሳካላቸው የሥነ ልቦና ጦርነት ፕሮግራሞች አንዱ ነው፡፡ ጥቁሮች ነጩን መሲህና ነጭ አምላክን እንዲያመልኩ በማስተማር በተያያዥ አንድም ነጮችን እንዲያመልኩ ወይም እንዲያደንቁ ማድረግ ተችሏቸዋል። ነጩ ኢየሱስ ለእኛ ለጥቁሮች ሞተ የሚለው የእምነት አስተምህሮ ትርጓሜም በጥቁሮች ስውር አዕምሮ ውስጥ ለነጭ መሲህ ባለውለታ ስሜት እንዲሰማው ማድረግ ዓላማው ነበር፡፡ ይህ ዓይነት የሃይማኖት ትምህርት ሒደት የአፍሪካን ባሪያዎች ታዛዥ፣ ትሁትና ለነጮች ጌቶቻቸው የበለጠ ታማኝ እንዲሆኑ ለማድረግ ተጠቅመውበታል፡፡

በሃይማኖታዊ መንገድ አዕምሮን የመቆጣጠር ሒደት የነጭችን አገዛዝ ዘላቂነት ያለው በማድረግ አፍሪካውያንን ታማኝ ባሪያዎች አድርጓቸዋል። በተጨማሪም ከአራት መቶ ዓመታት በፊት የተተገበረው የጥቁር ሕዝቦች አዕምሮን የመቆጣጠሪያ ስልት ሳይታረምና ሳይስተካከል ላለንበት ትውልድ ድረስ ደርሷል፡፡ አሁንም በሚሊዮኖች በሚቆጠር ጥቁር ሕዝብ አዕምሮ ላይ ተፅዕኖውን ማሳረፉ ቀጥሏል። በአሁኑ ጊዜ ብዙ የጥቁር አብያተ ክርስቲያናትን ስንጎበኝ ግድግዳዎቹ በነጭ አማልክት ሥዕሎች የተጌጡበት ምክንያት ይህ ነው።

ሆኖም ግን አፍሪካውያንን ከበርካታ ችግር የታደጉ መልካም ነጮችን አንዘነጋም፡፡ አፍሪካውያን ለሚገጥማቸው ችግር ሁሉ በርካታ ፍየሎችን በማረድና መስዋዕት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት በሚሞክሩበት ወቅት ለውኃ እጥረት የሚታረደውን ፍየል አስቀርተው ከከርሰ ምድር ውኃ ቆፍረው ያበረከቱ፣ ለበሽታ (በተለይ ለወባ) ለመሰዋት ይታረድ የነበረውን ፍየል አስቀርተው መድኃኒት ያቀረቡ ነጮችን ማንሳት እንችላለን በሚል ኬንያ ቶክ ዘገባውን ያጠናቅቃል፡፡ 

ከዚህ በፊት የግብጹ ፕሬዚዳንት ጋማል አብድል ናስር ‹‹እስራኤላውያን ከጥቁር ሕዝብ ምድር በሙሴ መሪነት ጥለውና ንቀው ከወጡ በኋላ ነጭ ሆነው ተመልሰው መጡ›› ማለታቸው ሳይዘነጋ፣ ‹‹እኔ ጥቁር ነኝ፣ ይሁን እንጂ ውብ ነኝ፣ ጥቁረቴ እንደ ቄዳር ድንኳኖች፣ እንደ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት መጋረጃዎችም ነው።  ጥቁር ስለ ሆንኩ ትኩር ብላችሁ አትዩኝ፣ መልኬን ያጠቆረው ፀሓይ ነውና›› (መኃልየ 1:5-6) መባሉን በመጥቀስ ‹‹አባቱ ሰሎሞን ጥቁር ነኝ ካለ ክርስቶስ ጥቁር ነው›› በሚል ባለንበት ወቅት በተለይም በቅኝ ግዛት በተያዙ የአፍሪካና በካሪቢያን አገሮች ያሉ ወጣቶች ዘንድ ሐሳቡ እየተቀነቀነ ይገኛል፡፡ እንደውም ‹‹ክርስቶስ ጥቁር ነው›› የሚለውን ሐሳብ የማጽናት አዝማሚያ ያዳበሩ አርቲስቶች በሥዕል ሥራቸው ይህንን በግልጽ አንጸባርቀዋል።

እንደዚህ መጣጥፍ አዘጋጅ አውሮፓውያኑ ክርስትናን ያለ አግባብ ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈጸሚያና ጥቅማቸውን ለማሳካት መንቀሳቀሳቸው ውጤቱ ከሌሎችም አልፎ የቅኝ ግዛት ወላፈን ያልነካት ኢትዮጵያ ድረስ መታየቱን ላወሳ እወዳለሁ፡፡ በአገራችን ላይ ያረፈው ተፅዕኖ ደግሞ ክርስቲያኑ በክርስቲያኑ ላይ በተቃርኖ እንዲነሳ በር የከፈተ በመሆኑ ወይም በሌሎች አፍሪካ አገሮች ‹‹አህዛብ ስለሆናችሁ በክርስትና ወደ ሕዝብነት እናምጣችሁ›› የሚል የነበረ ሲሆን፣ አገራችን ላይ ግን ክርስቲያን ነኝ ብሎ የተቀመጠውን ሕዝብ በአዲስ የክርስትና አስተሳሰብ ለማነወር የተሞከረበት በመሆኑ ተቃርኖውን ‹‹ክርስትናን በክርስትና ላይ›› ብለን ልንጠራው እንችላለን።

ተፅዕኖውን በጉልህ የተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስንና ክርስቲያን ለሚለው ስማቸው መሠረት የሆናቸውን ክርስቶስ ጨምሮ በሚጋሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶና በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ባለው ተቃርኖ ውስጥ ነው፡፡ አንድ ከኦርቶዶክስ ወደ ፕሮቴስታንት የመጣን ሰው፣ ‹‹ክርስቲያን ሆነ›› በሚል መገለጹ እንዳለ ሳንነካው፣ ሌሎች ሁለት ተቃርኖዋቸውን በማንሳት ጥያቄ እንጠይቃለን፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያኗ ቅዱስ መጽሐፉ እንዳለ ሆኖ የቅዱሳን ገድላት መጻሕፍትን አዋልድ (ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወለዱ ወይም ግብረ ቅዱሳንን፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ነብያትንና ራሱ መሲሁ ኢየሱስን መሠረት አድርገው የተጻፉ ወይም ታሪካቸው በተተረከበት አግባብ የተጻፉ) በማለት እንደ አግባቡ ጉባዔ ላይ ትሰብካለች፡፡ ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኗ ከቅዱሱ መጽሐፍ ውጪ ያሉ ታሪኮችን አብነት አታደርግም፡፡ ሆኖም  የአፍሪካውያኑ ወጣቶች ጥቁር ኢየሱስ የሚለው ጥያቄ በክርስትና ስም በአያት ቅድመ አያታቸው ላይ በደረሰው የታሪክ ቅሚያ፣ ግፍና በደል ተፅዕኖ ውስጥ ሆነው የሚያመነጩት እንደመሆኑ መጠን በአገራችን ያለውን የሁለቱ ቤተክርስቲያን ተቃርኖው ላይ ለማናቸውም ወገኖች መከራከር ባንችል እንኳን የጥቁር መንፈስ እንዳረፈበት ኢትዮጵያዊ አንዳንድ ጥያቄዎችን ለማንሳት ይጋብዛል፡፡

አንደኛ ‹‹ኢያሱ በገባዖት ፀሐይን አቆመ›› (ኢያሱ 10:12) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በኩራት ቆሞ የሚሰብክ ኢትዮጵያዊ የሃይማኖት መምህር›› አቡነ ዜናማርቆስ ምዕመኑን ቁርባን አቁርበው እስኪጨርሱ ድረስ ፀሐይ እንዳትጠልቅ ገዝተው (በፈጣሪ ስም አዘው) አቆሟት የሚለው የገድል ክፍል ለመዋጥ ሲቸግረውና ‹‹በሬ ወለደ ነው›› ሲል ስንሰማ፤ ሁለተኛ ‹‹አብርሃምን ዘርህን እንደምድር አሸዋ አበዛልሃለው አለው›› ዘፍጥረት (22:16) የሚለውን ክፍልንም ‹‹ለምን ይዋሻል? አይደለም የአብርሃም ዘር የሰው ዘር በሙላ ቢቆጠር የምድርን ይቅርና አንድ ሲኖ ትራክ አሸዋ ያክላል?›› ብሎ ሳይጠይቅ እንዲሁ ሲሰብክ እያየነው ‹‹አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቅድስናው እንደ መላዕክት፣ ክህነቱ እንደመልከጻዴቅ›› በሚል በገድሉ መገለጹን ሲሰማ ‹‹አቤት ዋቴ (ውሸት )›› ከማለት አንስቶ ‹‹ተረት ተረት›› ሲለው ‹‹ለአብርሃም ዘርህን እንደምድር አሸዋ አበዛልሃለው በሚል በተጻፈው ነገሩን የማጉያ የግነት አጻጻፍ ስልትን ተከትለው›› ገብረመንፈስ ቅዱስን ንጽሕናው እንደመላዕክት፣ ክህነቱ እንደመልከጻዴቅ›› በሚል በገድሉ መገለጹን እንዴት አልተረዳንም?

ሦስተኛ መምህሩ፣ ክርስቶስ ከሞት ሲነሳ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን እንዳወጣና ‹‹በእኔ ያመነ እኔ ያደረኩትንም ይሁን ከዚያም በላይ ሊያደርግ ይቻለዋል›› (ዮሐንስ 14:12) የሚለውን ቃል ያምናል፡፡ ሆኖም ክርስቶስ ሰምራ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን እንዳወጣች በገድሏ ሲዘከር ግን መሳለቅ ሲቀናው ተመልክተን፣ ‹‹ክርስቶስ ሰምራ በመጽሐፉ ቃል መሠረት አልፈጸመችውም? ለምን ለማመን ተቸገርን? ‘ሰው የጻፈው ነው’ ብለን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ተዘጋጀ? ከመነሻው እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ብሎ የሚነግረንስ ሙሴ አልነበር? ሙሴ የሚባል ሰው ራሱ መኖሩን እንዴት  አመንን? ሙሴስ ቢኖር ‹‹የተረከውን የውሸት ተረት ነው›› እንዴት ልንለው አልቻልንም? ሌሎቹ የመጽሐፉ ክፍሎችስ የነጠላ ቅዱስ መጻሕፍት ስብስብ አይደሉም? ጸሐፊዎቹስ ግለሰቦች አልነበሩም? ገድላቱንስ እንዴት እንደ አንዱ አድርገን አልተቀበልነውም? እንዴት የሰው የፈጠራ ድርሰት ልንለው ቻልን? በቅዱስ መጽሐፍ የተጻፈውን የቅዱሳን ታሪክ የተቀበልንበትና ያመንበት ምክንያቱ ምንድን ነው? እንዴት አልተጠራጠርነውም? ካልተጠራጠርነው የገድላትን ታሪክ እንዴት ማመን አልቻልንም? ጥቁር ሊደግመው አይቻለውም? ባናምነውም እንዴት ማንቋሸሽ ተቻለን? ካልተቀበሉ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱሱንም መሆን የለበትም? የጥቁር ቅዱስ የለውም?  ጥቁር ሕዝብ ለቅድስና አልታደለም? ምልከታው የአውሮፓውያኑ የሥነ ልቦና ተፅዕኖስ የወለደው እንደሆነ መመልከት አንችልም? ነገሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ከዚህ በፊት ጠይቀነው በማናቀው መልኩ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥያቄ እንድናነሳበት አይጋብዝም? የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭራል፡፡

ሁለተኛው የአብያተ ክርስቲያናቱ ተቃርኖ በምሥጋና መዝሙር ላይ ጎልቶ የሚታይ ሲሆን መዝሙሩ ምን ዓይነት ይሁን? ቅኝቱ ምን ይሁን? የማመሥገኛ መሣሪያዎች ምንድን መሆን አለባቸው? የሚሉትን ያካትታል፡፡ ስለዚህ ተቃርኖ በስፋት የዳሰሰው የከተማው መናኝ በሚል የአቀናባሪ ኤልያስ መልካን የሕይወት ታሪክ በጥልቅ ትንታኔ የዳሰሰው የይናገር ጌታቸው (ማዕረግ) መጽሐፍ ነው፡፡

‹‹የቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ፅዮንን ይዞ መምጣት በአይሁድ ማኅበረሰብ የተለመዱ የዝማሬ ሥርዓቶች ወደ አገራችን እንዲገቡ በር ከፍቷል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገን የታሪክ አጋጣሚውን ለመረዳት ከሞከርንም በጊዜው ይቀርብ የነበረው መዝሙር በመሰንቆ፣ በበገና፣ በዋሽንት፣ በከበሮና በጽናጽል የታጀበ ነበር›› የከተማው መናኝ ገጽ 144፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከብሉይ ወደ ሐዲስ ኪዳን ከተሸጋገሩ ጥቂት ቤተክርስቲያን አንዷ ናት፡፡ በዚህ ምክንያት ክርስትና ወደ አገሪቱ ሲገባ ለምስጢራተ ቤተክርስቲያን ማስፈጸሚያ የሚሆን ዜማ አልተቸገረችም፡፡ …ከስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኋላ ግን ነገሮች ተቀያይረዋል፡፡ ቀላል የሚባሉ የዜማ ድርሰቶችን ተሰናብታ ውስብስብና ከፍ ያሉ ድርሰቶችን ወደ መጠቀም ተሸጋገረች፣ የቅዱስ ያሬድን መምጣት ሲያስገነዝብ›› (የከተማው መናኝ ገጽ 145)፡፡

‹‹በሃያኛው ክፍለ ዘመን የፕሮቴስታንት ዕምነተ ተከታዮች ቁጥር እየበረከተ የሄደ ሲሆን የኢትዮጵያ የሆኑ የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጠቀም እንደነውር ተቆጥሯል፡፡… ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ጋር በብዙ መንገዶች ተለያይተዋል፡፡ በአገራችን የተለመዱ የመዝሙር ሙዚቃ መሣሪያዎችንም ባልተጻፈ ሕግ ከአገልግሎቱ አግዷል፡፡ በምሽት ቤቶች ሰው የሚመሰገንባቸው ናቸው ያላቸውን መሰንቆና ከበሮ ለእግዚአብሔር ክብር ማዋል አይገባም በማለት የምዕራቡን ዓለም መሣሪያዎች ተጠቅሟል›› (የከተማው መናኝ ገጽ 147)፡፡

‹‹የፕሮቴስታንቱ ሥርዓተ አምልኮ ከኢትዮጵያ ዜማዎች ተኳርፎ ለዘመናት ቢጓዝም ሙሉ ዘመኑን ግን ለዚህ እስረኛ አልሆነም፡፡ በመሆኑም ትዝታ ቅኝት ውስጥ የሚያርፉ ዜማዎችን በመድረስ ከውጪ ዓለም ተፅዕኖ ለመላቀቅ ሞከረ፡፡ በ1970ዎቹ መጀመሪያ የባህል የሙዚቃ መሣሪያዎች ተፅዕኖ ጎልቶ የሚታይባቸው ድርሰቶች እየተደረሱ በካሴት ታተሙ፡፡ ይሁን እንጂ ነገሩን እንደ ነውር በመቆጠሩ ሥራዎቹ በቀላሉ ተቀባይነት ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ እንደውም በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት አዝማሪዎች ለርኩሰት አገልግሎት የሚጠቀሙትን መሰንቆ ለእግዚአብሔር ምሥጋና ማቅረቢያ የተጠቀሙ ዘማሪያን ሊነወሩ ይገባል ተባለ›› (የከተማው መናኝ ገጽ 149)

ይህንን ተቃርኖ እንደ አንደኛው የሃይማኖት ተቋም ሆነን ሳይሆን የጥቁር ዘር እንዳረፈበት ኢትዮጵያዊ ወጣት መሰንቆን የኃጢዓት መከወኛ አድርጎ ጊታርን ለጽድቅ ለማዋል የተኬደበት መንገድ ቢያስደንቀንም ሰዎች አይደለም ከውጪ የመጣውን ሃይማኖት፣ ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስማምተው ከመከተላቸው ተሻግረው፣ ‘ከውጪ የመጣው ሃይማኖት የመጣበትን አገር የባህልና የፖለቲካ ፍላጎት ይዞብን ይገባል’ ያሉት ቻይናውያን በአንድ ወቅት የወሰዱትን ዕርምጃ ተመልክተን ነገሩን እናዳብረው፡፡

ከሂንዱይዝም ተገንጥሎ የወጣው ቡድሂዝም መነሻው ሰሜን ምሥራቅ ህንድ አገር ነበር፡፡ ታዲያ ቡድሂዝም ወደ ግቢዋ ሊገባ ከደጇ ሲያንጃብብ የተመለከተችው ቻይና ‘የህንድ መንግሥት ፍላጎትንም አዳብሎ መግባቱ አይቀሬ ነው’ በሚል በ400 ዓመተ ዓለም የነበረውን የራሷን ታዋቂ የሥነ ጽሑፍ ሰው ታአዎ ቲ ቺንግ መነሻ አድርገው፣ ተፈጥሯዊ ሕግና ትዕዛዝን ያቀፈ ታዎ ወይም ዳዎ የሚል አስተሳሰብ በማሳደግና ጣዎት በማድረግ፣ ታዎኢዝም (Taoism) በእያንዳንዱ ቻይናውያን ቤት እንዲመለክ አደረጉ፡፡ አገር በቀል ሃይማኖት መፈለጋቸው፣ ውሳኔያቸውን እዚያ ድረስ እንዲያስጉዙት አስገድዷቸዋል፡፡

እኛ ‘አገራችን የቻይናውያኑ ውሳኔ ደረጃ ትድረስ፣ አምላካችን የጉራጌ ቀደምት አምላክ ዋቅ ወይም ሃይማኖታችን የኦሮሞ ሕዝብ ቀዳሚ የሆነው የዋቄፈታ እምነት ብቻ ነው’ ባንልም ክርስትናው እኛን ይምሰል ማለቱ እንዴት ሊያቅረን ቻለ? ማመሥገኛ መሣሪዎቻችን እንዴት ሊረክሱብን ቻሉ? ከመሰንቆ ይልቅ ለጊታር ቅድስናን እንዴት ቸርነው? የአውሮፓውያኑ ተፅዕኖ ገደብ ባጣ መልኩ እንዴት ሊያጥለቀልቀን ቻለ? እኛው ጥቁር ሆነን የጥቁር የሆኑ ነገሮች እንዴት ሊረክሱብን ቻሉ? እንዴት ሰማይ ቤት እንደማያደርሰን አመንን? ምን ዓይነት ክፉ መርዝ አቀመሱን? ስለ ጥቁሩ ኢየሱስ ለማቀንቀን የተገደዱት ወጣቶችስ መነሻቸው እንዲህ ያሉ ነገሮች አልነበሩም ወይ? በኢትዮጵያ ወጣቶች ዘንድስ ሊቀነቀን ይገባዋል? በቀጣይስ መጽሐፍ ቅዱስን ተመልክተነው በማናውቀው መልኩ በቁራኛ እንድናስተውለው ይገባል? የሚሉ ጥያቄዎችን እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡

በተጨማሪም አውሮፓውያኑ በሃይማኖት ስም ባይደርሱብን እንኳን የሃይማኖት መምህሮቻችንን በመንፈሳዊ ኮሌጃቸው ለትምህርት ጋብዘው ቀይጠው የሚመግቧቸው አጀንዳ ባልታወቀ ሰዓት አፈትልኮ ሲፈነዳና በአንድ መቅደስ ሥር ያሉትን ሳይቀር በተቃርኖ ሲያቆም እንመለከተዋለን፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሥር ወንጌሉን በአግባቡ ተረድተው ትምህርት ይሰጣሉ ከምንላቸው መምህራን መካከል ቀሲስ መምህር ዘበነ ለማ (ዶ/ር) አውራው ናቸው፡፡ በ2014 ዓ.ም. በሰይፉ በኢቢኤስ ፕሮግራም ላይ ተጋብዘው ከሃተታው በመነሳት ብዙዎች ከኢትዮጵያ ፈላስፋ ወገን ስለሚመድቡት ዘርዓ ያዕቆብ (ወርቄን) ሲናገሩ ‹‹ዘርዓ ያዕቆብ ስለሚባል ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ይሁን ስለፍልስፍናው እንደማያውቁና ፍልስፍናው ምኑ ላይ እንደሆነ እንደማይገባቸው ተናግረዋል፡፡ በእርግጥ ‘ሐሳቦቹ የተዋህዶን ድንበር ጥሷል’ ከሚል ተነስተው የሰጡት አስተያየት ቢሆንም  መምህሩ እስከ ፒኤችዲ ዲግሪያቸውን በዘለቀው የቲዎሎጂ ትምህርታቸው ትሩፉቱ ከእርሳቸው አልፎ ለቤተክርስቲያን እንደተረፈ ብናምንም በትምህርት ሒደታቸው ውስጥ ከፈላስፋነት ይልቅ ለቅዠት የቀረበ ሥራ ያላቸውን አያሌ ፈላስፎችን መምህሮቻቸውና መጻሕፍት እንዳስተዋወቃቸው አንጠራጠርም፡፡ ሆኖም ግን ‹‹ዘርዓ ያዕቆብ የተባለ ፈላስፋ አላቅም ወይም ፍልስፍናው ምኑ ጋ ነው?›› በሚለው ሐሳባቸው ‘ኢያሱን ተቀብሎ አቡነ ዜና ማርቆስን አልቀበልም’ ካሉት ወገን በምን ይለያል? ሐሳቡን ባይቀበሉም የአገራቸውን ሰው በፈላስፋነት ለመቀበል ምን ገደዳቸው? በሐሳባቸው የጥቁርን ጥበብ ማነወሩ አልተስተዋለም? የአውሮፓውያኑ ተፅዕኖስ አፈትልኮ አልወጣም? የሚሉ ጥያቄዎችን ያጭራል።

በአፄ ዘድንግል የተቀላው ኢትዮጵያዊው መሲህስ የሐሳቡና የንጉሡስ የዕርምጃ መሠረት ከየት የመነጨ ነበር? የሚለውን በሁለተኝነት እናስከትላለን፡፡

ይቀጥላል….

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው habeshaw2022@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles