Friday, May 24, 2024

የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የወርቅ ማውጫ አካባቢን መቆጣጠራቸው ተሰማ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከዓመታት በፊት በቀድሞው ደቡብ ክልል በኩል 150 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትጵያ ድንበር ገብተው የሰፈሩት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች፣ ተጨማሪ 20 ኪሎ ሜትር ገፍተው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሱርማ ወርቅ ቁፋሮ ሳይትን መቆጣጠራቸው ተገለጸ፡፡

ታጣቂዎቹ የወርቅ ማውጫውን ከተቆጣጠሩ አንድ ወር ገደማ እንደሆናቸውና ወርቅ በማውጣት ሥራ እንደተሰማሩ፣ የክልሉ የሰላምና አስተዳደር ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት ክልሉ በባህላዊ መንገድ ሲያከናውን የነበረውን ወርቅ የማውጣት ሥራ እንዳቋረጠም የቢሮው ዋና ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰፊ ድንበር እንደሚጋራ የሚያስረዱት አቶ አንድነት፣ አሁን በታጣቂዎች የተያዘው መሬት በሱሪ ወረዳ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ወረዳው ማርዱር የሚባል ማዕከል የነበረው ሲሆን፣ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በሚያደርሱት ተደጋጋሚ ጥቃትና ዘረፋ የተነሳ የወረዳው ኪቢሽ ወደ የሚባል ሌላ ማዕከል ተዘዋውሯል፡፡ ኪቢሽ ከማንዱር እሰከ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ሲኖረው፣ የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በአጠቃላይ 150 ኪሎ ሜትር ድንበር ገፍተው ገብተዋል፡፡

‹‹ይህ ቀጣና ደቡብ ሱዳን ቀውስ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ የሬክ ማቻር ኃይል ይንቀሳቀስበት የነበረ ነው፤›› የሚሉት አቶ አንድነት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም ከሬክ ማቻር ጋር በነበረው ግንኙነት ምክንያት ታጣቂዎቹ ይንቀሳቀሱበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ መንግሥት እያወቀም የሬክ ማቻር ወታደሮች እስከ ሚዛን ተፈሪ ድረስ በመግባት ካምፕ አድርገው እንደነበርም አስረድተዋል፡፡

ይሁንና ደቡብ ሱዳን ውስጥ መረጋጋት ከመጣ በኋላ ከሬክ ማቻርም ከሳልቫኪርም የተጣሉ ኃይሎች የቀድሞው የሱሪ ወረዳ ማዕከል የነበረው ማርዱርን እንደያዙ መቅረታቸውን አቶ አንድነት ገልጸዋል፡፡ አክለውም ‹‹[ታጣቂዎቹ] ከማርዱርም አልፈው ዘረፋ ይፈጽማሉ፡፡ በቦታው ለከብቶቻቸው በረት ሠርተው በመሣሪያ ያስጠብቃሉ፡፡ በራሳችን አገር በማርዱር የእኛ አርብቶ አደር የግጦሽ መሬትና ውኃ መጠቀም አይችልም፡፡ ይህ ለረዥም ጊዜ ቆይቷል፤›› ብለዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን በኩል በተደረጉ ውይይቶች ዘረፋው “ረገብ” ብሎ እንደነበር ገልጸው፣ አሁን ተመልሶ እንቅስቃሴ መታየቱን አስታውቀዋል፡፡

ታጣቂዎቹ ከዚህ ቀደም ይዘው ከቆዩት 150 ኪሎ ሜትር መሬት በተጨማሪ 20 ኪሎ ሜትር በማለፍ፣ ባቻጌ በሚባል ቦታ ካምፕ ማድረጋቸውንና ይህም ወርቅ የሚወጣበት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ታጣቂዎቹ የታጠቁት መሣሪያ የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከሚይዙት ክላሽ የሚመጣጠን እንዳልሆነ አቶ አንድነት ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአንድ ወር ወዲህ ከማንዱር አልፈው የሱሪ ወረዳ የሆነው ኪሚሽ ከሚገኝበት 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ታጣቂዎች ካምፕ አድርገዋል፣ ወርቅ ማውጣትም ጀምረዋል፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹በፊት ድርቅ ሲኖር ከብቶቻቸውን ይዘው ለግጦሽና ለውኃ መጥተው ድርቁ ሲያልፍ ይሄዳሉ እንጂ፣ እንዲህ ቁጭ አይሉም፡፡ አሁን በመሬቱ ላይ እንደ ባለቤት ነው የሆኑት፤›› በማለት የአሁኑ ሁኔታ የተለየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ስላለው ሁኔታ ለፌዴራል መንግሥት ገለጻ መደረጉን የሚናገሩት አቶ አንድነት፣ ጉዳዩን በሰላማዊ ሁኔታ መፍታት እንዲቻል የንግግር መድረክ የመፍጠር አንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ከደቡብ ሱዳን ጋር በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ንግግር የማድረግ ልምዱ እንዳለ ገልጸው፣ ‹‹ንግግሩን ተከትሎ ከደቡብ ሱዳን ተገቢ የሆነ የማስተካከያ ዕርምጃ መወሰድ አለበት ብለን እናስባለን፤›› ብለዋል፡፡ ጉዳዩን በኃይል መፍታት የሚለው አማራጭ ሁለቱ አገሮች ካሉበት ሁኔታ አንፃር ተመራጭ እንዳልሆነ፣ ከደቡብ ሱዳን ጋር ሰላማዊ መንገድ መከተል የመንግሥት አቋም መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የድንበር ደኅንነትና አስተዳደር አገራዊ ስትራቴጂ አስፈላጊነትን አስመልክቶ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይም፣ ይህንን ጉዳይ አንስተው ከደቡብ ሱዳን ጋር የድንበር ማካለል ሥራ ባለመሠራቱ የተጋረጠውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን አሁናዊ የዳር ድንበር ማካለል ቁመና አስመልክቶ ገለጻ ያደረጉት ‹‹የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ያልተቋጨ የቤት ሥራ›› መጽሐፍ ጸሐፊ በለጠ በላቸው (ዶ/ር)፣ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው የድንበር ማካለል ሥራ ትኩረት እንዳልተሰጠው አስረድተዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን አገር ከሆነች አሥር ዓመት ቢያልፍም የጋራ የድንበር አካላይ ኮሚሽን እንዳልተቋቋመ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በጋምቤላና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች በኩል ከደቡብ ሱዳን ጋር የምትዋሰነው መሬት ሰፊ ሀብት ያለው በመሆኑ፣ ወደፊት ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -