Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለሀብቶች በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ የአፈር ማዳበሪያ እንዲያስገቡ ተፈቀደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጎማ ከመደረጉ በፊት ግዥ የፈጸሙ አርሶ አደሮች ገንዘባቸው ሊመለስ ነው

በዓለም አቀፍ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ የተነሳ ለዘንድሮ ምርት ዓመት ከፍተኛ ወጪ ያወጣው የግብርና ሚኒስቴር፣ ሰፋፊ እርሻ ያላቸው ባለሀብቶች በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ የአፈር ማዳበሪያ እንዲያስገቡ ፈቀደ፡፡

እስካሁን ባለው አሠራር የአፈር ማዳበሪያን ለማስመጣት ፈቃድ ያለው ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆነው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ሚኒስቴሩ አሁን በሰጠው ፈቃድ አቅሙ ያላቸው ባለሀብቶች የአፈር ማዳበሪያ ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች ባለሀብቶችም ማምጣት ይችላሉ፡፡

የአገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ሥርዓት በሀሉም ዘርፍ መንግሥት ላይ የተንጠለጠለ መሆኑን የሚያስረዱት በሚኒስቴሩ የግብርና ግብዓትና ግብይት ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ተስፋ፣ በየግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲውም የግል ዘርፉ የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ እንዲሳተፍ የሚፈቅድ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በዚህ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ በማድረግ የግሉ ዘርፍ እንዲሳተፍ ማድረጉን አስረድተው፣ ፖሊሲው ወደ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት መላኩን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ይሄ ፖሊሲ ባይፀድቅም የመንግሥትን ጫና ለማቃለል ሲባል፣ አስቀድሞ በሚኒስቴሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ውሳኔ ሰፊ እርሻ ያላቸው ባለሀብቶች ማዳበሪያ እንዲያስገቡ ተፈቅዷል፡፡

‹‹የግሉ ዘርፍ አባላት በተለያየ የገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ ተሰማርተው እያሉ፣ የአፈር ማዳበሪያ የሚጠይቁት ግን ከመንግሥት ነው፤›› ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ በራሳቸው የውጭ ምንዛሪ ለማስገባት አቅሙ ያላቸው ባለሀብቶች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በእርሻ የተሰማሩ ባለሀብቶች በዓመት ከ932 እስከ 970 ሺሕ ሔክታር መሬት የሚያርሱ ሲሆን፣ ከዚህም ከ18 እስከ 19 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ሰብል ይሰበስባሉ፡፡ አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች የሚያመርቱት ኤክስፖርት የሚደረጉ የቅባት እህሎች፣ ቡና፣ አኩሪ አተርና ቦለቄ ነው፡፡ ስንዴ እያመረቱ ለዱቄት ፋብሪካዎች የሚያቀርቡ ባለሀብቶችም አሉ፡፡

በአገር አቀፍ የማዳበሪያ አጠቃቀም ደረጃው በአንድ ሔክታር አንድ ኩንታል ዩሪያና አንድ ኩንታል ኤንፒኤስ ማዳበሪያ እንደሆነ የሚናገሩት በሚኒስቴሩ የእርሻ ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ገብረ ሥላሴ፣ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ግን ከዚህ በላይ የሚጠቀሙበት አጋጣሚ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

በዘንድሮው የምርት ዓመት ግን ባለሀብቶች ማዳበሪያ እየቀረበላቸው እንደ ቀድሞው መንግሥት ወደ አገር ውስጥ ከሚያስገባው ላይ ነው፡፡

የግብርና ግብዓትና ግብይት ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ እንደሚገልጹት፣ ሚኒስቴሩ የማዳበሪያ ማስመጣት ሥራን ወደ ግሉ ዘርፍ የማዘዋወር ዕቅድ አለው፡፡ ይሁንና ይህንን ለማድረግ በተፈለገው ጊዜ፣ መጠንና ተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ  ማዳበሪያ ማቅረብ የሚችል አካል እንደሚያስፈግል ጠቁመዋል፡፡

ይህ እስከሚሆን ድረስም መንግሥት በአነስተኛ ማሳ ላይ ተሰማርተው ላሉ አርሶ አደሮች የአፈር ማዳበሪያ ማቅረቡን እንደማያቋርጥ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በዘንድሮው ምርት ዓመት 15.1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ያቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 12.8 ሚሊዮን ኩንታል አዲስ የተገዛ ነው፡፡ ዘንድሮ ከተገዛው ውስጥ 11.2 ሚሊዮን ኩንታል ጂቡቲ ወደብ ደርሶ ከዚህ ውስጥ 93 በመቶ (10.4 ሚሊዮን ኩንታል) ወደ ክልሎች ተሠራጭቷል፡፡ በአጠቃላይም 5.6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ አርሶ አደሩ እጅ ገብቷል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት የተነሳ የማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ዋጋ መጨመሩን የተናገሩት አቶ መንግሥቱ፣ ባለፈው ዓመት እስከ 1,700 በር ሲሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዘንድሮ ዋጋው 4,500 ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ጭማሪ አርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል ብለዋል፡፡

በዚህም ምክንያት መንግሥት ባለፈው ሳምንት ባሳለፈው ውሳኔ የማዳበሪያ ግዥ የወጣው አጠቃላይ ወጪ 25 በመቶ ወይም 15 ቢሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል፡፡ ይህ ድጎማም አርሶ አደሩ ማዳበሪያ የሚገዛበትን ዋጋ በ1,100 ብር እንደሚቀንሰው፣ አሁን ግብይቱ እየተፈጸመ ያለው በዚሁ ዋጋ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ይህ የሚኒስቴሩ ውሳኔ የአፈር ማዳበሪያው መሰራጨት ጀምሮ ገበሬው ግዥ መፈጸም ከጀመረ በኋላ የተላለፈ በመሆኑ፣ በአማካይ በ4,500 ብር አንድ ኩንታል ማዳበሪያ የገዙ አርሶ አደሮች አሉ፡፡ ውሳኔው የተላለፈው ቀድመው የገዙ አርሶ አደሮችንም አካቶ መሆኑን የገለጹ አቶ መንግሥቱ፣ ‹‹የዘር ወቅታቸው ቀድሞ የነበረና በውድ የገዙ አርሶ አደሮች ገንዘባቸው እንዲመለስ እናደርጋለን፡፡ እንዴትና በምን መንገድ ይመለስ የሚለው እንደ ክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ይወሰናል፤›› ብለዋል፡፡

እስካሁን ድረስ አርሶ አደሮች የ5.6 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ መፈጸማቸው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች