Sunday, May 19, 2024

ማንነትን መሠረት ያደረገ ግድያ ወደ እርስ በርስ መጠፋፋት እንዳያመራ ተሰግቷል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ቀረበ

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማንነት መሠረት ያደረገ ኢሰብዓዊ ግድያ በአስቸኳይ ካልቆመ፣ ወደ ለየለት የእርስ በርስ መጠፋፋት እንዳያደርስ በእጅጉ እንዳሳሰበው ሥጋት እንደፈጠረበት አስታወቀ፡፡

      ምክር ቤቱ ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ዜጎች በሕይወት የመኖር ሰብዓዊ ዓለም አቀፋዊና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ሳይሸራረፍ እንዲከበር መንግሥትን አበክሮ ጠይቋል፡፡

የማንኛውም መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የአገርን ሰላምና የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ እንደሆነ ቢታወቅም፣ መንግሥት በዳተኝነቱ ምክንያት ግዴታውን በተሟላ መንገድ እየተወጣ አለመሆኑን፣ የምክር ቤቱ የቀድሞ ዋና ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ባነበቡት የማኅበሩ መግለጫ ተገልጿል፡፡

‹‹የዕለት ጉርስ እንኳን ያልተሟላለት ሕዝቦችን በሰላም ወጥቶ የመግባትም ሆነ በሕይወት የመኖር ዋስትና ፈጽሞ ከማይታሰብበት ደረጃ ደርሷል፤›› ያሉት ራሔል (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕዝብ በማንነቱ ተለይቶ እንደ መስዋዕት በግ በነፍጥ አንጋቢዎች ለዕርድ እየቀረበ ይገኛልና ይህንን እኩይ ተግባር በአጽንኦት እናወግዛለን፤›› ብለዋል፡፡

ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ በዜጎች ላይ በተፈጸመው አስነዋሪና ፀያፍ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ሕፃናት፣ ሴቶችና አረጋውያን በማንነታቸው ተለይው በጅምላ መጨፍጨፋቸውን ምክር ቤቱ አስታውሷል፡፡

በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በቡርጂ፣ በአማሮ፣ በደራሼ፣ በጉጂና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች በማንነት እየተለዩ በቤታቸውም ሆነ በማሳቸው እንደ አውሬ እየታደኑ መገደላቸው እንዳሳሰበቻው ራሔል (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የሰሜኑ ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ወከባ፣ ሕገወጥነት፣ እስራትና ግድያ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ምክር ቤቱ፣ በየአካባቢ በሚደርሱ ጥቃቶች ዜጎች ወላጆቻቸውንና ጧሪ ቀባሪዎቻቸውን እንዳሳጣቸው፣ ቤት ንብረቶቻቸው መውደማቸውን፣ መዘረፉን፣ መቃጠላቸውንና ኑሯቸው መመሰቃቀሉን ራሔል (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ባለበት አገር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለምግብና ለቁሳቁስ ፍላጎታቸው፣ ለሰብዓዊ ክብራቸው የመኖር ዋስትናን የሚያረጋግጡበት አንዳችም መንገድ አለመኖሩን መግለጫውን በመጥቀስ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እንደ ሰው በራሳችን ቀን እስክንሞትና እስክንጠፋ ድረስ በእንቅልፍ ውስጥ እንኳ የማይረሳ ሕመም በልባችን ይመላለሳል፡፡ ቁጭት፣ የሥነ ልቦና ጉዳት፣ ስሜታዊ ውጥረት፣ አለመደማመጥና መሸነፍ በሕዝብ አስተሳሰብ ላይ ድርብ አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል›› ብለዋል፡፡

ሕዝብን ያላማከለ አጀንዳ ያነገቡ የተለያየ ዓላማና ግብ ያላቸው ኃይሎች፣ የመንግሥትን ዝምታና ቸልተኝነት ደጀን በማድረግ ማንም ሊገታቸው የሚችል ተከላካይ ኃይል አለመኖሩን ሲገነዘቡ፣ አመቺውን ጊዜ እየተጠቀሙ በንፁኃን ዜጎች በተለይም በሴቶች፣ በሕፃናትና በአረጋውያን ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ ጅምላ ጭፍጨፋ እያካሄዱ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡

‹‹ምድራችን ከምንጊዜም በላይ በንፁኃን ደም ተጥለቅልቃ የነፍሳት የሲቃ ጣር በነፍሳችንና በመንፈሳችን እያቃጨለ ይደመጣል፣ መንግሥት ግን ለሕዝቡ ዋይታና ሰቆቃ ጆሮ አለመስጠቱ በእጅጉ አሳስቦናል፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም የመንግሥት የፀጥታና የደኅንነት ተቋማት በተሰጣቸው ሕዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት መሠረት፣ ወቅቱን የጠበቀ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ነቅሰው በማውጣት፣ በሕዝቡ ሰላምና በአገሪቱ ሉዓላዊነት ላይ የተጋረጡትን አደጋዎችን ቀድመው ሊከላክሉና ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳሰስበዋል፡፡

መንግሥት በፍፁም ቅንነትና ቁርጠኝነት ለሕዝብ ደኅንነትና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት፣ የንፁኃን ሞትና ሲቃ ወቅታዊ ፍትሕ እንዲሰጥ የጠየቀው ምክር ቤቱ፣ በደል በፍትሕ ይተካል እንጂ በቀል ልብን እንደማይፈውስ ዜጎች ተገንዝበው፣ የአንዱ ጥፋት ለሌላው ሕይወት ላይሆን፣ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ታጣቂ ኃይሎች የቆሙበትን ፅንፍ ለቀው ወደ መሀል በመምጣት ቁጣን፣ ጥላቻንና ምሬትን ትተው ትውልድ ያድኑ ሲል ምክር ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱ አክሎም በሰሜን የኢትዮጵያ ክፍል የተቀሰቀሰው ጦርነት ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላም ጋብ ቢልም፣ አሁንም አለመቋጨቱንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሪቱ ዳግም ወደ ጦርነት የመመለስ ከፍተኛ ሥጋት ያለባቸው የጦርነት ምልክቶች እየታዩ እንደሆኑ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

 ኢትዮጵያን ዳግሞ ወደ ጦርነት የሚያስገቡ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ቆመው ጦርነቱ በድርድር እንዲቆም፣ የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ኃይሎች የሚጠበቅባቸውን ሊያደርጉ ይገባል ብሏል፡፡

ምክር ቤቱ በምዕራብ ወለጋ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ክልሎችና በሌሎችም የአገሪቱ ክልሎች በከፋ ሁኔታ ለተገደሉ ንፁኃን ወገኖች መታሰቢያ የሚሆን ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንዲታወጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን አጥብቆ ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -