Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያዊነት ለጥቃት አይጋለጥ!

ጥቃትን የፖለቲካ ትግል መሣሪያ ማድረግ በመለመዱ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ሥጋት ውስጥ ይገኛል፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ትግል ዓላማ በሰላማዊና በሕጋዊ መሠረት ላይ መከናወን ሲገባው፣ ማንነትን መሠረት ያደረጉ በርካታ ጥቃቶች ተከፍተው በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን በግፈኞች ተነጥቀዋል፡፡ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በትግራይና በሌሎችም አካባቢዎች የተፈጸሙ ግድያዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ኢትዮጵያን ሰላም አልባ አድርገዋል፡፡ ለዘመናት የተገነቡ የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶች እየተናዱና ኢትዮጵያውያን በገዛ ወገኖቻቸው እየተጨፈጨፉ፣ ሰላምና መረጋጋት ሲጠፋ ተጠቃሚው ማን እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ ለሌላ ፍላጎት የሚደረግ ፉክክርን ሰላማዊና ሕጋዊ ከማድረግ ይልቅ፣ በንፁኃን ደምና ዕንባ የሚወራረድ ትንቅንቅ ኢትዮጵያዊነትን ለጥቃት እያጋለጠ ታሪካዊ ጠላቶችን የልብ ልብ እየሰጠ ነው፡፡ በሕዝብ ስም በመነገድ ትግልን ከጥቃትና ከጭፍጨፋ ጋር ያቆራኙ ሴረኛ ፖለቲከኞች ከድርጊታቸው ይቆጠቡ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጥቃት ሲከፈትበት ታሪካዊ ጠላቶች የበለጠ ይጠናከራሉ፡፡ እነሱ የሚጠናከሩት ኢትዮጵያን አፍርሰው ታሪካዊ የሚሉትን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ነው፡፡

አገር የምትከበረውና የምትታፈረው በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሙሉ ፈቃደኝነት ሲኖር ነው፡፡ ዜጎች ከራሳቸው በላይ ለዚህች ታሪካዊት አገር በጋራ መቆም ሲችሉ ነው፡፡ ከስግብግብነትና ከአሻጥረኝነት ምንም አይገኝም፡፡ የደመኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ ትርፉ ሞት፣ ስደት፣ ውድመትና ትርምስ እንደሆነ በሚገባ ታይቷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ ውስጥ የሚገባው በግልጽነትና በነፃነት መነጋገር ሳይቻል ሲቀር ነው፡፡ ግልጽነት በሌለበት ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ ነፃነት በሌለበት የሚከተለው ነውጥ ነው፡፡ የማይደማመጡ ፖለቲከኞች መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ጥላቻና ቂም በቀል በሚናኝበት ደግሞ ውዥንብር የበላይነቱን ይይዛል፡፡ መተማመን ጠፍቶ ሕገወጥነት ይበረታል፡፡ ነገር ግን ለሕግ የበላይነት በመገዛት ለአገር ህልውና ሲባል ከውዥንብሮች ውስጥ መውጣት የሚቻለው በመነጋገር ነው፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ ደግሞ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ምሁራንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ከጥላቻና ከመፈራረጅ ዳዋ ውስጥ በመውጣት መነጋገር መለመድ አለበት፡፡ ውዥንብርና ትርምስ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ታሪካዊ ጠላቶች የሚፈልጉት ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተባልተው አገራቸውን እንዲያፈርሱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት፡፡ ከ115 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት የብዙኃን አገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ መንግሥት፣ የመከላከያና የደኅንነት ኃይል፣ የፋይናንስ ሥርዓት፣ በአስተማማኝ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የሚመራ የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርና፣ የኢንቨስትመንት፣ የንግድ፣ ወዘተ ሥርዓት ያስፈልጋታል፡፡ በሚገባ የተደራጁ የዴሞክራሲ ተቋማትና የሲቪል ማኅበረሰቦች ሊኖሯት ይገባል፡፡ አስተማማኝ የፍትሕ ሥርዓት መኖር አለበት፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ አገር እስከሚያስተዳድረው መንግሥት ድረስ ለሕግ መገዛት ተገቢ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሰፍኖ በሕግ የታወቁ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ እነዚህን መብቶች የሚጠይቁ ዜጎችም በሕጉ መሠረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ይጠበቃሉ፡፡ በዚህ መሠረት አገር ስትራመድ ግጭት መቀስቀስና መጋደል ተረት ይሆናል፡፡ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ተፈጥሮ በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ይለመዳል፡፡ የዜጎች ሕይወትም በሰበብ በአስባቡ እንደ ቅጠል አይረግፍም፡፡ ነፃነቱን የሚያውቅ ዜጋ መብቱንና ግዴታውን ሲረዳ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት አያቅትም፡፡ ኢትዮጵያ ከድህነትና ከተዋራጅነት ተላቃ ሕዝቧ በነፃነት መኖር የሚችለው፣ ከአገራቸው በፊት ራሳቸውን የማያስቀድሙ ልጆቿ በትጋት ሲሠሩ ነው፡፡ አንገትን ቀና አድርጎ ለመራመድ የሚቻለው እንዲህ ሲታሰብ ነው፡፡

በዚህ ዘመን አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አገር የምትከበረውና የምትታፈረው፣ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የሚገነባ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ሙሉ ፈቃደኝነት ሲኖር እንደሆነ ሲታወቅ ነው፡፡ ዜጎች ከራሳቸው በላይ ለዚህች ታሪካዊት አገር በጋራ መቆም ሲችሉ ነው፡፡ ከስግብግብነትና ከአሻጥረኝነት ምንም አይገኝም፡፡ የደመኝነትና የጥላቻ ፖለቲካ ትርፉ ሞት፣ ስደት፣ ውድመትና ትርምስ ብቻ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ የሚገነባው ደግሞ በግልጽነትና በነፃነት መነጋገር ሳይቻል ሲቀር ነው፡፡ ግልጽነት በሌለበት ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ ነፃነት በሌለበት የሚከተለው ነውጥ ነው፡፡ የማይደማመጥ ሕዝብና መንግሥት መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ጥላቻና ቂም በቀል በሚናኝበት ደግሞ ውዥንብር የበላይነቱን ይይዛል፡፡ መተማመን ጠፍቶ ሕገወጥነት ይበረታል፡፡ ለሕግ የበላይነት መገዛት ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ለሕግ የበላይነት መስፈን ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ከጥላቻና ከመፈራረጅ ውስጥ በመውጣት ለሕግ የበላይነት መገዛት መለመድ አለበት፡፡ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ መከላከል የሚቻለው ሕግና ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ ዋስትና በአንድነት መቆም መቻል ነው፡፡ ይህ አንድነት የተለያዩ ማንነቶችን፣ ባህሎችን፣ ቋንቋዎችን፣ እምነቶችንና የመሳሰሉ ልዩነቶችን የሚያከብር ሲሆን ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአገሩ ክብርና ዘለዓለማዊነት በጋራ ይቆማል፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረ የአገር ፍቅር ስሜት ይበልጥ አብቦ የበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ትገነባ ዘንድ ቅንነትና በጎ ፈቃድ ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በአምባገነንነት አስተሳሰብ ስላልሆነ፣ ለዴሞክራሲያዊ እሴቶች መገዛት ተገቢ ነው፡፡ ለአገር የማይጠቅሙ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ለዚህ ዘመን ትውልድ ስለማይመጥኑ አሽቀንጥሮ መጣል ይገባል፡፡ በብሔርተኝነት ካባ ውስጥ የአገርን ህልውና የሚንዱ ተግባራትም ሆኑ፣ ማናቸውም ፀረ ኢትዮጵያ ድርጊቶች ፋይዳ የላቸውም፡፡ ከዚህ ይልቅ በሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ግንኙነት ማስፈን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የሚፈልገው ሰላም፣ ፍትሕ፣ ዕድገት፣ በእኩልነት ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖር ነው፡፡ ከጋራ እሴቶቹ የሚመነጩትም በአንድነት መቆም፣ የጋራ ግብና ራዕይ ይዞ ከትውልድ ወደ ትውልድ መቀባበል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፀንታ የምትቆመው በዚህ መንገድ ነው፡፡

የንፁኃን ደም በከንቱ ከፈሰሰ በኋላ በሐዘን ከንፈር ከመምጠጥ ይልቅ፣ በንፁኃን ደም እጃቸውን የሚታጠቡትን በሕግ የመጠየቅ ዕርምጃ ላይ ማተኮር ይመረጣል፡፡ ይህ ዕርምጃ ተጠያቂነት እንዳለ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ ተጠያቂነት በመጥፋቱ ምክንያት ብቻ ከክልል ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ በየሥልጣን እርከኑ የተንጠላጠሉ ሕገወጦች አገር ሲያተራምሱ ዝም ማለት አይገባም፡፡ በሕግ የበላይነት የሚያምኑ ንፁኃን ዜጎችን ሕገወጦች በጠራራ ፀሐይ ሲጨፈጭፉና ሲያፈናቅሉ በቸልታ መመልከት፣ አገርን የማትወጣው ቀውስ ውስጥ መክተት ነው፡፡ ነጋ ጠባ የዕልቂትና የመፈናቀል መርዶ እየሰሙ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን መተማመን ያስፈልጋል፡፡ አስተዋዮቹና ኩሩዎቹ ኢትዮጵያውያን በመከባበርና በመተሳሰብ ከትውልድ ወደ ትውልድ ያሸጋገሯትን አገር፣ የጥፋት እጆች ሰለባ ማድረግ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ልጆቿ እኩል እናት መሆኗ የሚረጋገጥበት በሕግ የበላይነት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እየተቻለ፣ ሕገወጦች እሳት እየጫሩ እንዲያፈርሷት መፍቀድ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለጥቃት አይጋለጥ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ያቀረቡት መልቀቂያ ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰማ

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞው የውኃ ሀብት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...