Saturday, May 18, 2024

የተቋማት ሪፎርም ወይስ የተቋማት ልምሻ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፣ በመላ ኢትዮጵያ ወደ ሁለት ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኞች እንዳሉ አመልክቷል፡፡ በቅርቡ መተግበር በጀመረው ‹‹ጂኢጂ›› በተባለው የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ የተነሳ፣ ለመንግሥት ሠራተኞቹ የሚከፈለው ዓመታዊ የደመወዝ ክፍያ መጠን የ32 ቢሊዮን ብር ዕድገት ማስመዝገቡንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ መሥሪያ ቤቶች ከደመወዝና ከጥቅማ ጥቅም ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ ተቋማዊ ውጤታማነትን የሚያሳድጉና አቅም የሚያጎለብቱ በርካታ የአሠራር ማሻሻያዎች በየጊዜው ይተገበራሉ፡፡ እንደ ቢፒአር፣ ቢኤስሲና ኤቢኤም የመሳሰሉ የአሠራር ሥርዓቶች በመንግሥት ተቋማት መተግበራቸውን ሪፖርቱ የሚጠቃቅስ ሲሆን፣ በእነዚህ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገኘሁት ያለውን የኦዲት ጉድለትና የአሠራር ግድፈት ወደ መዘርዘር ይገባል፡፡

በመንግሥት ተቋማት አሁን ላይ ውጤት ተኮር ትግበራ እንደሚባለው ሁሉ የአቅም ግንባታ፣ የክህሎት ምዘና፣ ካይዘን፣ ወዘተ እየተባለ በሰው ኃይልም ሆነ በንብረት አያያዝና በአደረጃጀት በኩል የአሠራር ማሻሻያ ተደረገ መባሉ የተለመደ ሪፖርት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያ በተገልጋዮች ዕርካታ ይመዘን ከተባለ፣ ብዙ ችግር እንዳለበት ነው የሚነገረው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ አጠቃላይ ኢትዮጵያ ካለባት የተቋማት ግንባታ ሕመም ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አበበ አሳመረ የተቋማት የመጀመርያው መለኪያ የአገልግሎት ወጥነት ነው ይላሉ፡፡ ‹‹አንድ ዓይነት አገልግሎት መስጠት የተቋማት ቀዳሚው ተቋማዊ መገለጫ ነው፡፡ አንዱ ክፍለ ከተማ አሥር ብር ለአንድ አገልግሎት ከፍዬ፣ በሌላው ክፍለ ከተማ ለተመሳሳይ አገልግሎት 20 ብር የምጠየቅ ከሆነ፣ አድሏዊ አሠራር ተፈጽሞብኛል ማለት ነው፡፡ የሕግ እኩል ተፈጻሚ አለመሆን፣ ኢፍትሐዊነትና ሌላም ችግሮች እንዲህ ባሉ ቀላል የአሠራር ግድፈቶች የሚፈጠሩ ናቸው፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡ 

የሥነ ልቦና ምሁሩ ደራሲና የሚዲያ ሰው ኤርሲዶ ለንዴቦ (ዶ/ር) ግን፣ አገልግሎት ለማማረጥ የሚያስችሉ ጠንካራ ተቋማት አለመገንባታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ ‹‹መንግሥት፣ መንግሥት ነው›› የሚባለው በሕግ ሲመራ ወይም ‹‹Good Government is Government of Law›› ሲሉ ያስቀመጡት ኤርሲዶ (ዶ/ር)፣ ‹‹የውጭ ሰዎችን ስለተቋማት አስፈላጊነት ከመጠየቅ ይልቅ፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ሪፖርተር ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጾቹ የጻፋቸውን ጉዳዮች መከለሱ ጠቃሚ ነው፡፡ ተቋም፣ ተቋም፣ ተቋም፣ እየተባለ የሚወተወተው ለሁሉም ወገን የሚመች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ወሳኝ ነው ተብሎ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ካየነው ወደኋላ ነው የተጓዝነው፡፡ የነበሩን መንግሥት ሁሉ ተቋማት አስፈላጊ መሆናቸውን ቢናገሩም፣ ነገር ግን ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ላይ ግድ የላቸውም፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በዋናነት ጠንካራ ተቋም በኢትዮጵያ ከተገነባ፣ ሕዝብ ለመጨቆንና አገር ለመዝረፍ ስለማይመቻቸው ነው፤›› በማለት ኢትዮጵያ ያለፈችባቸውን ተቋማት መገንባት አለመቻል ውጣ ውረድ ጠቁመዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ባለሙያና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው፣ የተቋማት ግንባታን የሒደት ውጤት ነው ይሉታል፡፡

‹‹ተቋማትን ከመገንባታችን በፊት ከልማት፣ ከፍትሕ፣ ከዴሞክራሲ አንፃር ሲሆን፣ በተቋማቱ ሊፈቱ የሚችሉ አገራዊ ራዕዮችን ማስቀመጥ ግድ ይላል፡፡ ሁሉም ተቋማት የሕዝብ አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ፓርላማውን ጨምሮ ሲቪክ ማኅበራትና ሁሉንም የዴሞክራሲ ተቋማት ያካትታል፡፡ ምን ዓይነት አገልግሎት እየሰጡ የሕዝብን ፍላጎት ማርካት ይችላሉ የሚለው በአግባቡ መቀመጥ አለበት፤›› ሲሉም ያስረዳሉ፡፡   

አቶ መሱድ የተቋማት አገነባብ ሒደትን ሲያስረዱ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገንባት ወሳኝ የሆኑት እንደ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ዕንባ ጠባቂ፣ ዋና ኦዲተር፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ ሚዲያውና የትምህርት ተቋማት የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ በእነዚህ ዙሪያ ሚዛኑንና ርቀቱን የጠበቀ ተጠያቂነትን ያሠፈነ የሥልጣን ክፍፍል በማድረግ ነው አገር የሚገነባው፤›› በማለት ነበር ሐሳባቸውን የገለጹት፡፡  

ኢትዮጵያ ወጥ የሆነ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ከምትፈተንባቸው ምክንያቶች ውስጥ ጠንካራ ተቋማትን ማፍራት አለመቻሏ ቀዳሚው ነው ይባላል፡፡ በብዙ ተቋማት ግንባታ ሒደት በቅብብሎሽ መቀጠል የቻሉ፣ ተቋማዊ ትውስታና ማንነታቸውን ይዘው የዘለቁ፣ ወይም ባላቸው ይዞታ ላይ እሴት እየጨመሩ ራሳቸውን ያሳደጉ ተቋማት በኢትዮጵያ ጥቂት ናቸው ይባላል፡፡ ይህ የተቋማት ግንባታ መቆራረጥና ዘለቄታዊነት ማጣት ደግሞ መልሶ ኢትዮጵያን የሚጎትት ችግር መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚያሰምሩበት፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ አበበ አሳመረ፣ ‹‹በብዙ ተቋማቶቻችን ውስጥ የሚገጥመን አሠራር የሚያጉላላና የሚያሰቃይ ከመሆኑ የተነሳ፣ የትም ቦታ ምንም ነገር ገጥሞህ ባትሄድ ይሻላል፡፡ ተቋም ግንባታ ከሕግ አተገባበር ጋር፣ ተቋም ግንባታ ከፍላጎትና ከአቅርቦት ዕድገት ጋር፣ ተቋም ግንባታ በየጊዜው ከሚለዋወጠው ተቋማዊ መዋቅርና አሠራር ጋር የተሳሰረ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የመሬት አስተዳደርን ብትወስድ ሰባት ነው፣ ስምንት ጊዜ ተቀያይሯል፡፡ የመጀመርያው ለምን ፈረሰ? የሚነግርህ የለም፡፡ እንደገናም የመሬት ባንክ ለምን ተባለ? የሚነግርህ የለም፡፡ በየትም ብትሄድ የተቋማት ትውስታን ማቆየት የሚባል ነገር የለም፤›› በማለት ነው የሚናገሩት፡፡

አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው፣ ተቋማትን ውጤታማ ለማድረግ ያስፈልጋል ስለሚሉት ነጥብ ሲናገሩ፣ ‹‹ነፃነታቸውንና ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው በአግባቡ ማገልገል የሚችሉበትን የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ይጠይቃል፡፡ ተቋማት የሰዎች አስተሳሰብ ውጤት ናቸው፡፡ የሰዎች ሐሳብ የሚገራበት የሕግ ማዕቀፍ ከተቀመጠ በኋላ ዓላማቸውን ማሳካት እንዲችሉ፣ በበጀትና በቴክኒክ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ ጣልቃ ባለመግባት በማናቸውም መንገድ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኩል፣ በተለይ ዋናው የሥልጣን ባለቤት ፓርላማው ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል፤›› በማለት ነው የሚገልጹት፡፡ 

ኤርሲዶ ለንደቦ (ዶ/ር) ግን መንግሥት በግሉ ዘርፍ ሊሸፈኑ የማይችሉ ተቋማት ግንባታ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ነው የሚመክሩት፡፡ ‹‹ምዝበራ፣ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግርም ሆነ በተቋማት የሚታዩ ብልሹ አሠራሮች የሚስተዋለው መንግሥት ያለ አቅሙና በማያገባው እየገባ ሁሉንም እኔ ካልሠራሁ እያለ፣ ተቋማትን በመጠፍጠፉ የመጣ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹መሠረታዊና የአገር ምሰሶ የሆኑ ተቋማት የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት የሚጠብቁት ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ መከላከያና ደኅንነት ናቸው፡፡ የመንግሥት መሠረታዊ ሚና መሆን ያለበት 21 ሚኒስትሮችን መገንባት ሳይሆን ፖሊስ፣ ፍርድ ቤትና መከላከያን መፍጠር ነው፡፡ ከእነዚህ ውጪ ያሉ ሁሉም በግል ዘርፍ ሊሸፈኑ የሚችሉ ተቋማት ናቸው፡፡ መንግሥት በማያገባው እስከገባ ድረስ ግን ሙስናውም ሆነ የአስተዳደር በደሉ ሊቀረፍ አይችልም፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ መጣ ከተባለ ወዲህ ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ብዙ ለውጦች ተደርገዋል፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ወደ 22 ዝቅ ከማድረግ ጀምሮ በበርካታ ዘርፎች ብዙ ሽግሽጎች ተካሂደዋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ በየተቋማቱ በርካታ ሪፎርሞች መደረጋቸው ይጠቀሳል፡፡ ለአብነት ያህል በመከላከያ፣ በደኅንነትና በፍትሕ ተቋማት የተደረጉ ሪፎርሞች ብዙ ሙገሳና አድናቆት ሲቸራቸው መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ የሆኑት አቶ በላቸው ግርማ ግን፣ ከመከላከያም ሆነ ከደኅንነት የሚቀድሙ የአገር ምሰሶ የሆኑ ተቋማት አሉ ነው የሚሉት፡፡ ‹‹አሁን ያለንበት አገራዊ ሥነ ልቦና የሚወስነው ካልሆነ በስተቀር፣ በሰላሙ ጊዜ ቢሆን የመከላከያ መኖርም ጭምር ከእነ አካቴው ሊረሳ ይችላል፡፡ በሕግ የበላይነትና በዴሞክራሲ የተመሠረተ አገር እመራለሁ ካልክ መከላከያን የመሳሰሉ ተቋማትን ከኋላ ታደርጋቸዋለህ፡፡ የአገር ምሰሶ የሚባሉ ብዙ ተቋማት አሉ፡፡ የመንግሥት መሠረታዊ አካላት ከሚባሉት ከሕግ አውጪው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥሎ የፍትሕ አካላት ናቸው ወሳኝ የአገር ምሰሶዎች፤›› በማለት የሌሎች ተቋማትን ወሳኝነት አመልክተዋል፡፡ 

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፣ ከለውጡ ወዲህ ለተቋማት ግንባታ የተሰጠውን ትኩረት በሰፊው አውስተዋል፡፡ ‹ሐሳብ ሰውን ይገነባል፣ ሰው ተቋማትን ይገነባል፣ ተቋማት ደግሞ አገርን ይገነባሉ፤›› በማለት የተናገሩት ዓብይ (ዶ/ር)፣ ተቋማትን መገንባት ብቻ ሳይሆን ማጠናከር ለአገር ግንባታ መሠረት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

ከዚሁ ጋር አያይዘው ለአገር ወሳኝ በሆኑ ተቋማት ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ ባለፉት አራት ዓመታት ብዙ የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ እንደ መከላከያና ደኅንነት ባሉ መሥሪያ ቤቶች የተደረገውን ለውጥ በእጅጉ ሲያደንቁም ተደምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፍትሕ ተቋማትን በተመለከተ ከባድ ትችት ማቅረባቸው አነጋጋሪ ነበር የሆነው፡፡ ዳኛ፣ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስን የመሳሰሉ ተቋማትን ‹‹ሌቦች›› በማለት መጥራታቸው ደግሞ ያልተጠበቀና እስካሁንም አነጋጋሪነቱ የቀጠለ ጉዳይ ሆኖ ነው የከረመው፡፡

አቶ መሱድ በፓርላማው ስለፍትሕ ተቋማት የሰጡት አስተያየት ከጠቅላይ ሚኒስትር የማይጠበቅ ነው ይሉታል፡፡ ‹‹የማንኛውም ተቋም ሚና መጨረሻም ፍትሕ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ መንግሥትም የሚያስፈልገው ማኅበራዊ ፍትሕ ለማስፈን ነው፡፡ በማናቸውም ተቋማት ውስጥ ቢሆን ሰዎች ሊያጠፉ እንደሚችሉት በፍትሕ ተቋማት ውስጥም ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ ይህንን ሰውኛ ባህሪ ተቋማዊ በማድረግ በፍትሕ ተቋማት ላይ ሌባ ናቸው ብሎ ትችት ማቅረብ ግን እጅግ አደገኛ ነው፤›› ይላሉ፡፡ 

ሐሳባቸውን ሲያክሉም፣ ‹‹አገራችን የጀመረችውን ዴሞክራታይዜሽን፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ማዘመንና ማሻሻልም ሆነ የሕዝብ ቅቡልነት እንዲያገኝ የማድረግ ሥራ አስተያየቱ ያረክሰዋል፡፡ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ለፍትሕ ሥርዓት መቃናት ለውጥ እናመጣለን ብለው ቀን ከሌሊት ሲደክሙ በሀቅ የሚሠሩ ሰዎችንም አስተዋጽኦ ያኮስሳል፡፡ ፖሊሶችን ለምሳሌ ብናይ የኑሮ ሁኔታቸው የሚታወቅ ቢሆንም እኛን ለመጠበቅ ብርድና ፀሐይ ሳይሉ፣ ካምፕ ውስጥ እያደሩ፣ እየራባቸውና እየጠማቸው መሣሪያ ተሸክመው የሚንከራተቱ ዜጎች ናቸው፡፡ ዳኞች መዝገብ ተሸክመው ከቤት ቢሮ እየተንከራተቱ ቅዳሜ እሑድ ሳይሉ ሕግን ለመተግበር የሚጥሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ዓቃቤያነ ሕጎችም የወጣው የአገር ሕግ አለመጣሱን የሚከታተሉ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ጥፋት ቢገኝ በራሱ በውስጥ ባለ አሠራርና የተጠያቂነት አግባብ መጠየቅ ይቻላል እንጂ፣ በቀጥታ በቴሌቪዥን በሚሠራጭ የፓርላማ ቆይታ ላይ እነዚህን አካላት በደምሳሳው መወንጀል አግባብ አልነበረም፤›› በማለት ነው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ላይ ወቀሳ ያቀረቡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋማት ሪፎርም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሠራቱን በተናገሩበት አንደበት፣ በአንድ ወቅት እጅግ ውጤታማ የሆነ የተቋማት ሪፎርም ተደርጎባቸዋል ብለው ባደነቋቸው የፍትሕ ተቋማት ላይ መልሰው ትችት ማዝነባቸው በብዙዎች ዘንድ ትልቅ ግርምትን የጫረ ጉዳይ ነው የሆነው፡፡ በኢትዮጵያ በብዙ ተቋማት ውስጥ እንደሚታየው ፈተና ሁሉ በፍትሕ ተቋማት አካባቢም ችግር መኖሩን የሚከራከር ብዙም የባይኖርም፣ ነገር ግን በፍትሕ ተቋማቱ ላይ የቀረበው ትችት ብዙዎችን አላስደሰተም ማለት ይቻላል፡፡ ችግር ቢኖር እንኳን የተቋማቱን ችግር መቅረፍ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሚመሩት አስፈጻሚ አካል ሆኖ ሳለ፣ መንግሥትን ነፃ በማድረግ ተቋማቱን ብቻ መተቸቱ ያልተዋጠላቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ችግር ቢኖር እንኳ ችግሩ መነገር ያለበት በአደባባይ በሚደረግ የጅምላ ውንጀላ አለመሆኑን የተቹ ወገኖች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉትን ንግግር አጥብቀው ተቃውመውታል፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪ አቶ በላቸው ግርማ እሳቸውም በየጊዜው እንደሚገጥማቸው በመጥቀስ፣ በፍርድ ቤቶች ምንም ጉድለት የለም ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዳኞች ሌቦች ናቸው ብለው መናገራቸው እውነት ቢሆን እንኳ ጥያቄ እንደሚያስከትል ነው የሚጠቁሙት፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፖሊስና ስለዓቃቤ ሕግ ሌብነት መናገራቸው የራሳቸው አመራር ድክመት ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሁለቱም በእሳቸው ሥር የሚተዳደሩ ተቋማት ናቸው፡፡ የፍርድ ቤት ግን በተለየ ሁኔታ መታየት አለበት፡፡ መንግሥት ሲባል በአጠቃላይ ሦስት የሥልጣን ክፍፍል አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት አስፈጻሚ መንግሥት እንዳለ ሁሉ፣ ሕጉን የሚያወጣ ፓርላማ፣ እንዲሁም ሕግ የሚተረጉም ፍርድ ቤት አለ፡፡ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው ችሎት ላይ ካልሆነ ሊገናኙ አይችሉም፡፡ በፍርድ ቤቶች ስለሚሆነው አስፈጻሚው አይመለከተውም፡፡ ሌብነት አለ ከተባለም የሚመለከተው ተቋሙን በቀጥታ የሚከታተለው የፓርላማው ሥራ ነው የሚሆነው፡፡ ችግሩ ቢኖርም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩት መንገድ መነገሩ በከፍተኛ ሁኔታ የዳኝነት ነፃነትን ይጋፋል፡፡ ንግግራቸው ፍርድ ቤቶችም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር እንደሆኑ አድርጎ የመሣል ዝንባሌን በሕዝብ ውስጥ ይፈጥራል፡፡ ከሪፎርሙ በኋላ በፍርድ ቤቶች ላይ እያቆጠቆጠ ያለውን የሕዝብ አመኔታ መልሶ የሚጎዳና የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደርግ ነው፤›› በማለት ነው የኢትዮጵያን መሠረታዊ የተጠያቂነት ወሰን አጣቅሰው አቶ በላቸው ያብራሩት፡፡

ልክ እንደ እሳቸው ሁሉ የፍትሕ አካላት ላይ በአገር መሪ ደረጃ ትችት መቅረቡ ያልተዋጠላቸው የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ባለሙያው አቶ መሱድ በበኩላቸው፣ ‹‹የእሳቸው አስተያየት ያስከተለውን የተሳሳተ አመለካከት ለማቃናት ራሱ አድካሚ ነው ብዬ እገምታለሁ፤›› በማለት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውንጀላ ክብደት ያስቀምጡታል፡፡ ‹‹ከለውጡ በኋላ የፍትሕ ተቋማትን ጨምሮ በጣም ብዙ ሪፎርሞች ተደርገዋል፡፡ ተጠያቂነት ካለ ሕጋዊ ሥርዓትን ተከትሎ ጥፋት ፈጻሚ የሆኑ ግለሰቦችን መጠየቅ ይቻላል፡፡ ከዚህ ውጪ ተቋማቱን መፈረጅ ግን የተቋማት ግንባታውና ማዘመኑ ሥራ ላይ ውኃ የሚቸልስ ብቻ ሳይሆን እየሠሩ ማፍረስ ነው የሚሆነው፡፡

‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ለመናገር የተገፋፉበት ምክንያት ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በዚህ ልክ እንዲናገሩ የሚጋብዝ ጥያቄ ከፓርላማው ቀርቦላቸው ነበር ወይ? የሚለው ግልጽ አይደለም፡፡ ተቃዋሚውና አቃቂር ፈላጊው ብዙ በሆነበት አገር፣ እንዲህ ዓይነት ስህተት መፈጸም አግባብነት የለውም፡፡ ሰው ናቸውና ይሳሳታሉ ብሎ መውሰድ ይሻላል፡፡ ነገር ግን በእሳቸው ደረጃ ያለ ማንም ሰው ንግግሩ እንዲህ ዓይነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ ቢቻል መጠየቅ አለባቸው፡፡ አለበለዚያም ወጥተው በይፋ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፤›› በማለት ጭምር ነው አቶ መሱድ ጠንከር ያለ ወቀሳ ያቀረቡት፡፡

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ኢትዮጵያ ኢንሳይት በተባለ ድረ ገጽ ላይ፣ ‹‹የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ በኢትዮጵያ ወደ ፍትሕ ማዝገም›› በሚል ርዕስ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ በተለይም በፍርድ ቤቶች፣ በተቋማት አደረጃጀትና በሕጎቻቸው አካባቢ የተደረጉ የሪፎርም ሥራዎችን የፈተሸ ጥልቅ ጥናታዊ ጽሑፍ አቶ ልዑል እስጢፋኖስ አስነብበው ነበር፡፡ በፍትሕ ሥርዓቱ ከተደረጉ ሪፎርሞች መካከል በዳኝነት ተቋማት ላይ የተደረገውን ለውጥ አምና ሚያዝያ ወር ላይ “Reform and Rule of Law in Ethiopia” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የዌቢናር (በይነ መረብ) ውይይት መድረክ ላይ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ዘርዝረው እንደነበር ጸሐፊው በጽሑፋቸው ያስታውሳሉ፡፡

በዚህ ውይይትም የዳኝነት ተቋማት ነፃነት ተቋማዊና ሪፎርም ብቻ ሳይሆን፣ የዳኞችንም ነፃነት ማስፋት የሚጠይቅ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንቷ መጥቀሳቸውንም ጸሐፊው ያወሳሉ፡፡ እሳቸው ከመጡ ጀምሮ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ቁጥር ከሰባት ወደ 60 ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰው፣ የሴት ዳኞችን ቁጥር ወደ 26 ማድረስ መቻሉን ተናግረውም ነበር ይላሉ፡፡

ሕገ መንግሥታዊውን ድንጋጌ በመጣስ ሲፈጸም የቆውን የፍርድ ቤቶችን በጀት በመንግሥት የመወሰን ሒደት በማስቀረት፣ የፍርድ ቤት በጀት በቀጥታ በፓርላማው እንዲመደብ መደረጉን፣ በጀቱም ከ30 እስከ 40 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ወ/ሮ መዓዛ መናገራቸውን፣ በዚህ ዓመት የተመደበው በጀት አምና ከነበረው 660 ሚሊዮን ብር ወደ 970 ሚሊዮን ብር ማደጉን መጥቀሳቸውንም የልዑል እስጢፋኖስ ጽሑፍ ይተርካል፡፡

የሠራተኛ አስተዳደር ሥራዎች ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መዛወራቸው፣ የተጨማሪ ችሎቶች መቋቋም፣ የሕንፃዎችና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሞች መሻሻል ሌላው ለውጥ ሲሆን፣ ተነጥለው የቆዩ አስተዳደራዊ ሥራዎችን የሚሠሩ አጋዥ ሠራተኞችን ወደ ተቋሙ መመለሳቸውንም ከሪፎርሙ ውጤቶች መካከል ብለው አውስተዋል፡፡  ለዳኞችም ሆነ ለሠራተኞች ተከታታይ ሥልጠና መሰጠቱን በስኬት የተናገሩት ፕሬዚዳንቷ፣ ከዚህ በተጨማሪም ለዳኞች የተደረገው የደመወዝ ጭማሪ ብቻ ሳይሆን፣ የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ መደረጉንና ያለ መከሰስ መብታቸውም መረጋገጡን ስኬታማ ለውጦች ሲሉ ማስቀመጣቸውን ነው ጽሑፉ ያስነበበው፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም በእነዚህ ተቋማት የሚታዩ ችግሮች ገና መቀረፍ አለመቻላቸውን ነው ጸሐፊው እንደ ጉድለት ያወሱት፡፡ 

ጠበቃና የሕግ አማካሪ በላቸው፣ ‹‹ፍርድ ቤቶች ካጠፉ አይወቀሱ ለማለት አልችልም፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ሆኖም ሳይንሳዊ በሆነና በተጨበጠ መንገድ ትችቱ ቢቀርብ የተሻለና ለለውጥም ገንቢ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

‹‹በፍርድ ቤት ሙስና ተንሰራፍቷል›› ብሎ ፓርላማው ካሰበ፣ የሾሟቸውን ክብርት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊን ጠርቶ መጠየቅ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት የዳኝነት ነፃነትን መርህ ፍፁም የሚጋፋና የሚያደርስበትም ጉዳት የከፋ ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ በፖሊስ አካባቢ ድብደባ ይፈጸማል፡፡ ተያዙ ቢባልም ነገር ግን ፍርድ ቤት ቀርበው ውሳኔ ሲሰጥ አንሰማም፡፡ ልክ እንደዚህ ተድበስብሰው የቀሩ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በየአካባቢው አሉ፡፡ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ፍርድ ቤቶች ጠንካራ ካልሆኑ አደጋው ከፍተኛ ነው፤›› በማለት ነው አቶ በላቸው ያስረዱት፡፡ 

ኤርሲዶ ለንደቦ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አግባብ ነው አይደለም የሚለውን መጠየቅ ያለባቸው ሌባ ናቸው ተብለው የተፈረጁ ተቋማት ናቸው ሲሉ ነው ጉዳዩን በአጭሩ የዘጉት፡፡

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ እንዳሉትም፣ በፍትሕ ተቋማት ውስጥ ብዙ ሪፎርሞች መካሄዳቸውን በርካታ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአቶ ልዑል እስጢፋኖስ በቀረበው ጽሑፍ ላይ እንደተመለከተው፣ አምና ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ወ/ሮ መዓዛ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሠሩ ጥናቶች ተገልጋዮች 70 በመቶ የዕርካታ መጠን እንዳላቸው ያሳያሉ ብለው ነበር።

ባለፈው የበጀት ዓመት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ለ166,758 ጉዳዮች ዕልባት ለመስጠት አቅደው የነበረ ሲሆን፣ 171,276 ጉዳዮችን በመዳኘት ዕቅዳቸውን በ2.7 በመቶ አልፈዋልም ሲሉ ጸሐፊው መረጃ አጣቅሰው ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ በፖሊስና ሕግ ማስከበር ሥራዎች ላይ ጉድለት መኖሩን ጸሐፊው ይጠቁማሉ፡፡

ጸሐፊው በማጠቃለያቸው የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች በእርግጥም ዋና ዋና ችግሮችን በመቅረፍ ሒደት ላይ ቢሆኑም፣ የፍትሕ አካሉ መንግሥትን (የአስፈጻሚውን አካል) በመደበኛነትና በተሳካ ሁኔታ የሚመረምርበት ደረጃ ላይ መድረስ አለበት  ይላሉ፡፡ ‹‹የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በቅርቡ ለሁሉም ፍትሕ መስጠት ይችሉ ይሆናል፡፡ ይህ ግን ተከሳሹ መንግሥት እስካልሆነ ድረስ ብቻ ነው፤›› በማለትም ኮርኳሪ ነጥብ በማንሳት ሐሳባቸውን ይቋጫሉ።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -