Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለዱቤ ግብይት የመድኅን ሽፋን አገልግሎት መስጠት እንዲፈቀድ ተጠየቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የመድኅን ሽፋን ዓይነቶች በጣም ውስን መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ በተለይ የንግድ እንቅስቃሴውን ለማሳለጥ ወሳኝ የሚባሉ የኢንሹራንስ ዓይነቶች እየተተገበሩ አይደሉም፡፡ በኢትዮጵያ በዓመት ከሚሰበስበው የዓረቦን መጠን ከ65 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ከሞተር ወይም ከተሽከርካሪ ኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰበሰብ መሆኑ የኢንሹራንስ ሽፋን ውስንነቱን ያሳያል፡፡ ከሞተር ኢንሹራንስ ቀጥሎ ከፍተኛ ሽፋን የሚሰጣቸው የማሪን (የባህር ጭነት ትራንስፖርት)፣ ኢንጂነሪንግና የእሳት አደጋ የኢንሹራንስ ሽፋኖች ብልጫ ያላቸው ናቸው፡፡

ከእዚህ ኢንሹራንስ ሽፋኖች ሌላ ንግድ እንቅስቃሴ መሳለጥም ሆነ ለአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጠቀሜታ ያላቸው የኢንሹራንስ ሽፋኖች በኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበሩ ያለመሆናቸውን የዘርፉ ባለሙያዎች ጭምር ይመሰክራሉ፡፡  

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ቢተገበሩ ለንግድ እንቅስቃሴው ቅልጥፍናም ሆነ ለአገራዊ ኢኮኖሚው ዕድገት ሁነኛ ሚና እንደሚኖራቸው ከሚጠቀሱት የመድኅን ሽፋኖች አንዱ ለንግድ የሚሰጥ የመድኅን ሽፋን (ትሬድ ክሬዲት ኢንሹራንስ) ነው፡፡ 

ይህ በመላው ዓለም እየተተገበረ ያለው የኢንሹራንስ ሽፋን ለሁሉም የቢዝነስ ዓይነቶች የሚያገለግል፣ በሻጭና በገዥ መካከል የሚደረግ የዱቤ ግብይት ዋስትና እንዲኖረው የሚያስችል የመድኅን ሽፋን በመሆኑ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው እኚሁ የዘርፉ ተዋንያኖች ይገልጻሉ፡፡ 

ይህ የኢንሹራንስ ሽፋን ዓይነት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተተገበረ ባይሆንም አገልግሎቱ ይሰጥ ዘንድ ጥያቄው እየገፋ መምጣቱም ይጠቀሳል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዚህ የኢንሹራንስ ሽፋን ዓይነት መጀመር የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት፣ እንዲሁም ጥያቄዎቹ እየገፉ በመምጣታቸው በጉዳዩ ላይ ምክክር እንዲደረግበት አድርጓል፡፡ 

በዚህ የመድኅን ሽፋን አስፈላጊነት ላይ ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ መወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት የኒያላ ኢንሹራንስ አ.ማ. ዋና ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ መድኅን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ ሞላ፣ የንግድ መድኅን አገልግሎት (ትሬድ የክሬዲት ኢንሹራንስ) እጅግ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ በተለይ በዚህ ወቅት መተግበር ያለበት የኢንሹራንስ ሽፋን መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ዓለም እየተሻሻጠ ያለው በዱቤ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ያሬድ፣ ለዚህ የዱቤ ሽያጭ ደግሞ ራሱን የቻለ ክሬዲት ኢንሹራንስ መስጠት በሌላው የተለመደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዱቤ የተሰጠን ዕቃ በተገባው ኮንትራት መሠረት ባይከፈል ክሬዲት ኢንሹራንስ ሽፋን የገዛው ኩባንያ ያልከፈለውን ገንዘብ ለሻጭ እንዲከፍልለት የሚያስችል በመሆኑ በግብይት ውስጥ መተማመን እንዲፈጠር የሚያስችልም ነው፡፡ የኢንሹራንስ ዓይነቱ ገዥው በተለያዩ ምክንያቶች መክፈል ባይችል በሻጭ ላይ ለሚደርሰው ችግር ዋስትና የሚሰጥ፣ እንዲሁም በገንዘብ እጥረት ሊስተጓጎሉ የሚችሉ ግብይቶች በቶሎ እንዲፈጸሙ የሚያስችል እንደሆነ የአቶ ያሬድ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡

የኢንሹራንስ ሽፋኑ የንግድ የፖለቲካ ሥጋት (ኮሜርሻልና ፖለቲካ ሪስክ) በሚል የሚሰጥ ሲሆን፣ በኮሜርሻል ሪስክ የዋስትና ክፍያው የሚከፈለው በገዥው ችግር ምክንያት ወይም የመክፈል አቅም ባለመኖሩ ዕቃውን ወስዶ በራሱ መክፈል ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ 

ፖለቲካል ሪስክ ጋር በተያያዘ ሊከፍል ላልቻለ የዱቤ ሽያጭ ዋስትና የሚሰጥበት ሲሆን፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት ብዙ ዓለም አቀፍ ግብይቶችን ለመፈጸም ይህ ዓይነቱ የመድኅን ዋስትና ዓይነት እየተጠየቀ መሆኑን አቶ ያሬድ ገልጸዋል፡፡ በጦርነቶች፣ በዕገዳዎች፣ በማዕቀቦች፣ በመንግሥት በሚወጡ ሕጎችና በመሳሰሉ ምክንያቶች ከነጋዴዎች ቁጥጥር ውጪ በሆኑ ፖለቲካዊ ምክንያቶች ለሚከሰት የክፍያ መስተጓጎል የክሬዲት ኢንሹራንስ ሽፋን ለግብይት ተዋናዮች ዓይነተኛ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

በትሬድ ክሬዲት ኢንሹራንስ ውስጥ ወደ ሰባት ዓይንት የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች (የመድኅን ሽፋን አገልግሎቶች) ያሉት መሆኑን የሚገልጹት አቶ ያሬድ፣ አንድ ኩባንያ ለሙሉ ምርቱ የዱቤ አገልግሎት የኢንሹራንስ ሽፋን ከመስጠት አንስቶ በተለያየ መጠን የኮንትራት ዓይነት ዋስትና የሚያገኝበት ዕድልን እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ 

ትሬድ ክሬዲት ኢንሹራንስ ለሁሉም የቢዝነስ ሰዎች የሚያገለግል፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ባሉ ኩባንያዎች መካከል የሚደረጉ የዱቤ ሽያጮችንም ሆነ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር ለሚደረጉ ግብይቶች ሁሉ የሚሠራ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የክሬዲት ኢንሹራንስ ጥያቄ የሚያቀርበው ሻጩ መሆኑን፣ ገዥው ዕቃውን ከወሰደ በኋላ ባይከፍል በእሱ ምትክ የኢንሹራንስ ኩባያው ብድሩን እንደሚከፍል አስረድተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የመድኅን ሽፋኖች የማይከፍልበትን ምክንያትም አብራርተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ክሬዲት ኢንሹራንስ በጣም አስፈላጊና በኢትዮጵያ ሊተገበር የሚገባው አገልግሎት መሆኑን አስምረውበታል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የበለጠ ክፍት እየሆነች ስትሄድ ይህ የኢንሹራንስ ሽፋን ዓይነት የግድ ሊሆን ይገባልም ብለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ያሬድ፣ አገልግሎቱን ለመጀመር ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን የሕግ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በተለይ አሁን ላይ በዲቫሉዌሽን (ከብር የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል) በፖለቲካ አለመረጋጋትና በመሳሰሉት ምክንያቶች የተነሳ ብዙ ሻጮች ክፍያ እንደማያገኙ በመሥጋት የዱቤ ሽያጭ አገልግሎትን ስለማይሰጡ ግብይት መቀዝቀዙን ተናግረዋል፡፡ ይህ የመድኅን ሽፋን አገልግሎት ተጀምሮ ቢሆን ግን ኢኮኖሚውን በማነቃቃት በተገበያዮች መካከል መተማመን በመፍጠር፣ ሕጋዊ ግብይቶች እንዲጎለብቱ ያደርጋል ብለዋል። በመሆኑም ይህ የመድኅን ሽፋን በኢትዮጵያ በሥራ ላይ እንዲውል ሁሉም የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ 

በዕለቱ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢንሹራንስ ክትትል ቡድን መሪ አቶ ተስፋ ብዙአየሁ በቀረበው ሐሳብ ላይ እንደሚስማሙ ገልጸው፣ ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ ለማንኛውም የኢንሹራንስ ሽፋን ዓይነት ሕግ እንደማያወጣ ጠቅሰዋል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኢኖቬቲቭ የሆኑ አዳዲስ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎችን ወይም የመድኅን ሽፋን ዓይነቶችን ቀርፀው ለመተግበር እንደሚችሉ፣ በዚህ ረገድ የብሔራዊ ባንክ ሚና የኢንሹራንስ ተቋማቱ የሚያቀርቡትን አዲስ የኢንሹራንስ ሽፋን የአዋጭነት ጥናት በመገምገም አዋጭነቱ አረጋግጦ ፈቃድ መስጠት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ አገልግሎት ዙሪያ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አገልግሎቱን መስጠት ከፈለጉ የአዋጭነት ጥናት አድርገው ፈቃድ እንዲሰጣቸው ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረብ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል። 

አቶ ያሬድ ከዚሁ ጋር አያይዘው በተለያዩ የቦንድ ዓይነቶች ዙሪያ እየተሰጡ ያሉ የኢንሹራንስ ሽፋኖች ንግድና ግብይትን ለማሳለጥ እያገዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ እነዚህም የኢንሹራንስ ሽፋኖች ለጨረታ ማስከበሪያ ሰነድ (ቢድ ቦንድ) ፐርፎርማንስ ቦንድ (የመልካም ሥራ አፈጻጸም)፣ ሜንቴናንስ ቦንድ፣ ሰፕላይ ቦንድና ከስተም ጋራንቲ (የጉምሩክ ዋስትና) ቦንድ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከስተም ጋራንቲ ቦንድ በመቋረጡ አገልግሎቱ እየተሰጠ አለመሆኑን፣ ከመቋረጡ በፊት የተገቡ ውሎች ብቻ ለጊዜው እየተሠራባቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ለቢዝነሰ እንቅስቃሴ ቅልጥፍና ዓይነተኛ ሚና ያላቸው ክሬዲት ጋራንቲ ቦንድና ፋይናንሻል ጋራንቲ ቦንድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በፍፁም እንዳይሰጡ መከልከላቸውን አቶ ያሬድ አስታውሰዋል፡፡ ለግል ብድር እንዲሁም እርስ በርስ ለመበዳደር ይሰጥ የነበረው የፋይናንሻል ጋራንቲ ቦንድ፣ እንዲሁም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲከፍሉ የሚታዘዙ ቦንዶች ክልከላ እንደተደረገባቸው ገልጸዋል፡፡ 

እነዚህ በገበያ ውስጥ የነበሩ የዋስትና ዓይነቶች ክልከላ የተደረገባቸው አሠራሩ ባልተገባ መንገድ ሲተገበር በተፈጠሩ በርካታ ችግሮች ነው፡፡ ‹‹ሁሉም ነጭ ወረቀት ከኢንሹራንስ እየወሰደ የሚፈልገውን በርካታ ሚሊዮን ብር ከባንክ እየወሰደ ያልተከፈሉ በጣም ብዙ ብድሮች በመከማቸታቸው ሒደቱ ብሔራዊ ሥጋት ደረጃ ላይ በመድረሱ ብሔራዊ ባንክ የከለከላቸው ናቸው፤›› ያሉት አቶ ያሬድ፣ የእነዚህ የዋስትና ቦንዶች መከልከል ግን በኢኮኖሚው ውስጥ ብዙ ችግር ማስከተሉን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ክልከላው ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን ገቢንም እንደጎዳ ገልጸዋል፡፡ 

ከኢንሹራንስ የሚሰጥ ጋራንቲ ቦንድ (የቦንድ ዋስትና) ዓረቦን ተከፍሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ወደ ንግድ ባንኮች በማቅረብም ብድር ይወስድበታል፡፡ ይህ ዓይነት ዋስትና ኩባንያዎች ጥሬ ገንዘብ በመያዣነት ሳያቀርቡ ሥራ መሥራት የሚያስችላቸው በመሆኑ ለአጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴው ጠቃሚ ነበር ይላሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንዶች ይህንን አሠራር ባልተገባ መንገድ በመጠቀማቸው ለክልከላ ዳርጎታል፡፡ በዚህ ክልከላ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዳው የኮንስትራክሽን ዘርፉ መሆኑን የሚገልጹት የኢትዮጵያ ኮንትራክተሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሀብተ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም የፈለጉትን ያህል ጋራንቲ ይወስዱ የነበሩ ኮንትራክተሮች የፈጠሩት ቀውስ ለሌሎች ኮንትራክተሮችም ተርፏል፡፡ ቀድም ሲል በነበረው መንግሥት ወቅት እንደፈለጉ የሚሆኑት ኮንትራክተሮች የቅድሚያ ክፍያዎችንና በብድር የወሰዱትን ገንዘብ ሁሉ ይዘው መሠወራቸውን፣ በዚህ ምክንያትም ባንኮች ይህንን አገልግሎቱን እንዳይሰጡ መደረጉ ሌላው ኮንትራክተር ተጎጂ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁንም በዚህ ክልከላ ምክንያት ብዙ ኮንትራክተሮች ጨረታ ለመጫረት እንደተቸገሩ በመግለጽ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ በእንደዚህ ዓይነት ቦንዶች ላይ የጣለውን ክልከላ ቢያነሳ ሁሉም ተጠቃሚ እንደሚሆን ገልጸዋል።

አቶ ያሬድ በበኩላቸው ከዓለም አቀፋዊ ሁኔታ አንፃር እንዲህ ዓይነት ክልከላ ብዙ ላያስኬድ እንደሚችል፣ ነገር ግን ክልከላው ይነሳ ሲባልም ቀደም ሲል እንደነበረው ልቅ መደረግ እንደሌለበት፣ በጥንቃቄና በተጠና ሁኔታ ቢተገበር ኢኮኖሚውን የሚጠቅም በመሆኑ ቢፈቀድ መልካም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በእነዚህ ቦንዶች ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ባንክ ያልተመለሰና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቱ በማመዘኑ የተከለከለ ቢሆንም፣ በአግባቡ አገልግሎቱን ይጠቀሙ የነበሩ በተለይ ኮንትራክተሮች በእጅጉ ተጎጂ መሆናቸውን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባው ደግሞ አቶ ግርማ ይናገራሉ፡፡ ሌሎች በፈጸሙት ስህተት መጎዳት የለባቸውም ይላሉ፡፡

በተለይ ክልከላ የተደረገባቸው ቦንዶች ከዚህ ቀደም በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ መዋላቸው ተገቢ ያለመሆናቸውን አስረድተው፣ ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል መልሰው ሥራ ላይ ቢውሉ መልካም መሆኑን አቶ ያሬድ ይገልጻሉ፡፡

አቶ ግርማ፣ ‹‹ይህ ጉዳይ ብዙ ኮንትራክተሮችን እየጎዳ ያለ በመሆኑ ብሔራዊ ባንክ እንዲያነጋግረን በደብዳቤ ጭምር ላቀረብነው ጥያቄ መልስ አልሰጠንም፤›› ብለዋል፡፡ ማኅበራቸው ግን በኮንትራክተሩ ላይ ጫና እየፈጠረ ያለው ክልከላ ሊነሳ እንደሚገባ ማኅበሩም መደመጥ እንዳለበትም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ አሰግድ ገብረ መድኅን ደግሞ የትሬድ ክሬዲት ኢንሹራንስ በቶሎ መተግበር ካለባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በተለይ ወደ ስቶክ ማርኬት እየተገባና የውጭ ኩባንያዎች መግባት ጋር ተያይዞ ይህ የመድኅን ሽፋን ዓይነት ዕገዛ ተደርጎም ቢሆን ሥራ ላይ መዋል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡  

በዕለቱ ውይይት የተደረገባቸው የትሬድ ክሬዲት ኢንሹራንስና የብሔራዊ ባንክ ክልከላ የተደረገባቸው የቦንድ ዓይነቶች፣ ለኢኮኖሚው የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍተኛ በመሆኑ ሥራ ላይ መዋል ያለባቸው ናቸው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች