Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ገዥው ፓርቲ ሕግ ካላከበረ ሌላው ሊያከብር አይችልም›› መብራቱ  ዓለሙ (ዶ/ር)፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ

የኢትጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሐሙስ ሰኔ 16 ቀን 2014 .ም. ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ በጉባዔው ማጠናቀቂያ የምክር ቤቱን ሥራ አስፈጻሚዎች በአዲስ ተክቷል፡፡ በዚህ ምርጫ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የቦሮ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባልናአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ መብራቱ ዓለሙ ዶ/ር የምክር ቤቱ ዋና ሰብሳቢ በመሆን ተመርጠዋል፡፡ ሲሳይ ሳህሉ አዲስ ከተመረጡት ዋና ሰብሳቢ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡– እስቲ ስለራስዎ ይንገሩን፣ የፖለቲካ ሕይወትዎ ምን ይመስላል?

ዶ/ር መብራቱ፡አሁን የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል ነኝ፡፡ ፓርቲው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ከተቋቋመ ገና ሦስት ዓመቱ ነው፡፡ በዚህ ፓርቲ ውስጥ የሥራ አስፈጻሚ አባል፣ የውጭና ዓለም አቀፍ ግንኙነነት ኃላፊ ስሆን፣ በተካሄደው የፖለቲካ ፓርቲዮች የጋራ ምክር ቤት ምርጫ በዋና ሰብሳቢነት ተመርጫለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ምርጫው እንዴት ነበር የተካሄደው? እንዴት ወደ እዚህ ኃላፊነት መጡ?

ዶ/ር መብራቱ፡ከዚህ በፊት በኃላፊነት የነበሩ አባላት የሥልጣን ዘመን ሁለት ወራት ያለፈው ቢሆንም፣ በአሠራሩ መሠረት በየሁለት ዓመቱ የሥራ አስፈጻሚዎች ምርጫ የሚካሄድ ስለሆነ እሱን ጠብቆ የተካሄደ ነው፡፡ እስካሁን በምክር ቤቱ ውስጥ በአቅም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ አባልነት እሠራ ነበር፡፡ በተጨማሪም በምክር ቤቱ ውስጥ የነበረኝ እንቅስቅሴ ጥሩ ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ከራሴ ፓርቲ ሥራ በተጨማሪ ማለት ነው፡፡ በዚህ ኃላፊነት አገር እንድትቀጥል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅንነትና በእኩልነት በማገልገል፣ በተለያዩ ፓርቲዎች መካከል የሐሳብ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳ አገርን ማስቀደም ላይ አተኩሬ እሠራለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲሱ ኃላፊነት ምን የተሻለ ነገር ይዘው ይመጣሉ?

ዶ/ር መብራቱ፡በእርግጠኝነት እንደ አንድ የጋራ ምክር ቤት ስብስብ በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰቱ ያሉ የፀጥታ ችግሮች ብዙ በመሆናቸው፣ ንፁኃን ያለ ምንም በደላቸው እየተገደሉ ስለሆነና የፖለቲካ ምኅዳሩም እየጠበበ በመምጣቱ፣ በቀጣይ ምኅዳሩን የማስፋትና የዜጎች መብት ጥሰት እንዴት መቆም እንደሚኖርበት በጥናት ላይ ተመሥርተን መሠረታዊ ችግሩ ምንድነው? የፖለቲካ ፓርቲዎች ለአገር ምን ማድረግ አለባቸው? መንግሥትስ እንዴት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት? በማለትና ጫና በማሳደር ለውጥ እንዲመጣ አበክረን እንሠራለን፡፡ ከፍተኛ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ ግን በዋነኝነት የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ በተለይም ሰላምና ፀጥታ ላይ ምክር ቤቱ ከተለያዩ ድርጅቶችና ከመንግሥት ጋር በመሆን፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማሳተፍ በጋራ እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡– ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የዜጎች ሞትና እንግልት እየበረታ መጥቷል፡፡ መግለጫ አውጥታችሁ ከማውገዝ ባለፈ ምን ዓይነት ሥራ ልትሠሩ ትችላላችሁ?

ዶ/ር መብራቱ፡- እንግዲህ አሁን በጋራ ምክር ቤት ውስጥ የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ተወካይ ጭምር በአስፈጻሚነት ተካተዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ለጋራ ምክር ቤቱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በተለይ ገዥው ፓርቲ በአስፈጻሚነት መካተቱ መሬት ላይ ያለው ችግር ምንድነው የሚለውን ለመረዳት፣ ችግሮችን ለማየትና መልስ ለመስጠት ይረዳናል፡፡ ሁለተኛ በመግለጫ ብቻ ችግር አይፈታም፡፡ ስለዚህ ምክር ቤቱ የሚያስበው አገራዊ የጋራ ምክክሩ ሁለት ነገሮችን ይዞ ይመጣል የሚል እምነት አለን፡፡ በተለይም ምክክሩ ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ ከተካሄደ ማለት ነው፡፡ አንደኛ አሁን በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን፣ መፈናቀሎችን፣ ግድያዎችን ስደቶችን ማስቆም የሚያስችለው አገራዊ ምክክሩ ነው የሚል ዕሳቤ አለ፡፡ ይህ ማለት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሳተፉበትና ግጭት ውስጥ የገቡ ተፋላሚ ኃይሎች ወደ አገራዊ ምክክር ጠረጴዛ ዙሪያ መጥተውና ጥያቄዎች አቅርበው መፍትሔ ሲሰጣቸው፣ ችግሩ ይቀርፋል የሚል እምነት አለን፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ ዘላቂ የፖለቲካ ሽግግር እናካሂዳለን ብለን እንጠብቃለን:: በዚህ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ በተለይም ምክክሩ አሁን ከተካሄደ እንደ አገር ማነቆ የሆነ ጉዳዮች ይስተካከላሉ ብለን እናስባለን፡፡ የመንግሥት መዋቅር ምን መምሰል አለበት የሚለው ጉዳይ በአገራዊ ምክክሩ ላይ ተነስቶ ምሁራን ይሳተፋሉ፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ምሁራን ፖለቲከኞች ተቀራርበው አገርን የሚያድኑ የመፍትሔ ሐሳቦችን ይዘው በመቅረብ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ የሚል እምነት አለን፡፡ የሲቪክ ማኅበራትም እንዲሁ  የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ይሠራሉ፡፡ በዚህ ረገድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ካልተረባረቡ ኢትዮጵያ የገባችበትን ቀውስ በቅርቡና በቀላሉ ማስወገድ ስለሚከብድ፣ የጋራ ምክር ቤቱ በሚገባ አተኩሮ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን በአገሪቱ የሚታየው ቀውስ መነሻ ምንድነው ብላችሁ ታስባላችሁ?

ዶ/ር መብራቱ፡- በግሌ በዚህ ጉዳይ የሚኖረኝ አስተያየት ኢትዮጵያ ውስጥ ተደረገ የተባለው ለውጥ እንደሚባለው ወደ ታች ወርዶ ተግባራዊ ሆኗል ወይ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ለውጥ የተባለው ጉዳይ የተወሰነ ቦታ ላይ አልተንሰራፋም ወይ የሚል የራሴ ግምት አለኝ፡፡ ለውጥ የተባለው ነገር ማኅበረሰቡ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡ የሚፈልገውንና የመዋቅር ጥያቄ መልሷል ወይ የሚለው ለእኔ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ በደንብ መሠራት አለበት፡፡ ምክንያቱም ለውጡ ወደ ታች አልወረደም፡፡ የታችኛው ቀርቶ የላይኛው መዋቅር ላይ በሚገባ የሚተገበር አይመስለኝም፡፡ ይህች አገር ብዙና ትልቅ ሕዝብ፣ እንዲሁም ብዙ ሀብት ያላት አገር በመሆኗ ከሀብት አጠቃቀምና ከብሔሮች መብት ጋር ተያይዞ፣ በተጨማሪም ከዜግነት መብትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጋር በተገናኘ ብዙ ክፍተቶች አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የታሪክ ትርክት ላይ አልተስማማንም፡፡ በአገራችን ታሪክ ላይ እንኳን መስማማት ያቃተን ሕዝቦች ነን፡፡ ከዚህ አለፍ ስትል በባንዲራ መስማማትም አልቻልንም፡፡ እንግዲህ በብዙ ጉዳዮች አልተስማማንም ካልን፣ ይኼን ሁሉ ጉዳይ ወደ አንድ ሊያመጣ የሚችለው የጋራ ምክክር ኮሚሽኑ በመሆኑ፣ በጋራ ምክክሩ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል አስተያየቱን እንዲሰጥና የዚህችን አገር ዕጣ ፈንታ እንድንወስን ጥሪ አቀርባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡-  ምክር ቤቱ በጋራ ምክክሩ ላይ ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር መብራቱ፡- የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችና ግንኙነቶች አሉ፡፡ እኔ ዛሬ የሰብሳቢነት ሚና ተቀብያለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ከኮሚሽኑ፣ ከመንግሥትና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር በመቀራረብ እንዴት ብንሄድ ይሻላል? በየት በኩል ብንንቀሳቀስ ለውጥ ልናመጣ እንችላለን? የሚለውን ዕቅድ አውጥተን እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡–  የሰሜኑን ክፍል ጦርነት ተከትሎ የሕወሓት አመራሮችና የፌዴራል መንግሥቱ ሊያደርጉት ስላሰቡት ንግግር ምን መረጃ አላችሁ? እናንተን ምንስ እያደረጋችሁ ነው?

ዶ/ር መብራቱ፡- እኛ ግልጽ የሆነ መረጃ የለንም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ ብዥታን የሚፈጥር ነው፡፡ በተለይ መንግሥት በእርግጥም ወደ ድርድር ገብቷል ወይ የሚለውን ጉዳይ በግልጽ አልነገረንም፡፡ ነገር ግን ምልክቶች አሉ፡፡ እኛም እያልን ያለው ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ውይይት እንዲመጡና በዚች አገር ዕጣ ፈንታ ላይ እንዲወያዩ ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ኃይሎች ሳይሳተፉ ሰላምና መረጋጋት ይመጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ጦርነት ለማስቆም ተፋላሚ ኃይሉ በሙሉ ውጊያ ማቆም አበለት፡፡ ስለዚህ ሸኔም ይሁን ሕወሓት ወይም ሌሎች ታጣቂ ኃይሎች ለምሳሌ የጉሙዝ ታጣቂዎች አሉ፡፡ በጋምቤላ በኩልም የተወሰነ ነገር አለ፡፡ እንዲሁም በደቡብ ክልል ደራሼና አማሮ አካባቢ ስትሄድ በርካታ ተፋላሚ ኃይሎች ያሉበት አገር ሆኗል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ኃይሎች ማስቆም የሚቻለው አንደኛ በባህላዊ የአገር ሽምግልና በስምምነት፣ በዕርቅ፣ በእርስ በርስ ንግግር ወይም በሌሎች ጉዳዮች ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የመጨረሻ ማሰሪያው አገራዊ ምክክሩ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሁሉም አካል ወደ ምክክር እንዲመጣ እንደ ምክር ቤት እንሠራለን፡፡

ሪፖርተር፡- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሲመሠረት የጋራ ምክር ቤቱ ይስተካከሉ በሚላቸው ጉዳዮች ላይ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ በርካታ ፓርቲዎችም ይስተካከል የሚሉትን ጉዳይ እየነቀሱ ሲጠይቁ ሰንብተዋል፡፡ አሁን ቅሬታ በተነሳባቸው ጉዳዮች ላይ የተደረሰ ስምምነት አለ?

ዶ/ር መብራቱ፡- ባለፈው ጊዜ የተወሰኑ ፓርቲዎች አንሳተፍም ብለው ነበር፡፡ በዚያው ልክ ደግሞ አብዛኞቹ ፓርቲዎች ይህች አገር ሌላ አማራጭ የላትም በሚልና ይህ ጉዳይ በስንት ጊዜ የተገኘ ዕድል በመሆኑ፣ ዕድሉን ተጠቅመን አገራችን እናሻግራለን የሚል አቋም ይዘዋል፡፡ ምክር ቤቱም ይህንን የብዙዎቹን አቋም ይደግፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡ በመንግሥት ላይ ከውጭ አገሮች ጫና በዝቷል የሚለውን ጉዳይ እንደ ጋራ ምክር ቤት እንዴት ይታያል?

ዶ/ር መብራቱ፡አሁን ጫናው እንደ በፊቱ አይደለም፡፡ በተወሰነ ደረጃ ቀለል የማለትና የመርገብ ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ምናልባት ሰሞኑን ከተፈጠሩት ግድያዎች ጋር ተያይዞ ሌሎች ነገሮች ተፈጥረው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሜሪካም ሆነች ማንኛውም አገር በሰጥቶ መቀበል እንቅስቃሴ ዲፕሎማሲው ላይ በጋራ የሚሠሩበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ ጉዳይ ዋነኛ ባለቤት መንግሥት በመሆኑ ዞሮ ዞሮ ይህች አገር ከማንኛውም አገር ጋር በበጎና በሚያስማሙ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ከጎረቤትም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር የሚኖራት ግንኙነት ሰላማዊ መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ሰላማችንና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እስካስጠበቀ ድረስ አብሮ መሥራት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ያ ሁኔታ ባልተፈጠረበት ወቅት መንግሥት የሚወስዳቸው የራሱ ዕርምጃዎች ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡ ከጦርነቱ በተጨማሪ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለመግታት እየሄደበት ያለውን መንገድ እንዴት ይገመግመዋል?

ዶ/ር መብራቱ፡- የኑሮ ውድነቱን በተመለከተ መንግሥት በተለያዩ መግለጫዎች እንደሚገልጸው፣ መቆጣጠር ያቃተው ነገር ቢኖር የኑሮ ውድነቱ ነው፡፡ የኑሮ ውድነት በሁለቱ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል፡፡ አንደኛው በምርት አቅርቦት ላይ ችግር ሲኖር ነው፡፡ ምርት በአብዛኛው በጦርነት፣ በድርቅና በመሰል ችግሮች ሳቢያ የሚጠበቀውን ያህል ማግኘት አልተቻለም፡፡ ምናልባት በስንዴ ላይ የተጀመረው ሥራ በበጎ ጎን ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ይህ ጅማሮ ግን ወደ ሌሎች ምርቶች ቢዞር በተሻለ የገበያ መረጋጋት መፍጠር ይቻላል፡፡ ሌላው ጉዳይ በፍላጎት ረገድ የሚታየው ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የምርት ፍላጎት አለ፡፡ በተለይም የሕዝብ ቁጥር መጨመር ከምርት ፍላጎት ጋር አብሮ እያደገ የሚሄድ በመሆኑ፣ ፍላጎት ከአቅርቦት ከበለጠ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ ይሄዳል፡፡

ሌላው ምክንያቱ ከውጭ የሚፈጥረው ጫና ነው፡፡ በተለይም በሩሲያና በዩክሬን የተከሰተው ጦርነት በማዳበሪያ፣ በስንዴ እንዲሁም በነዳጅና በምግብ ዘይት ላይ ትልቅ የሆነ ጫና ፈጥሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግብይቱ የሚመራበት ሥርዓት ውጤታማ አይደለም፡፡ ስለዚህ የንግድ ሥርዓቱን ማዘመን፣ ከዚያም ተቋማዊ ለውጦች መታየት አለባቸው፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ገንዘብ እየለቀቀ ያለው ወደ ንግድ ማኅበረሰቡ በመሆኑ፣ የዋጋ ንረትን ለማባባስ የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን የፋይናንስ ተቋማት ገንዘብ ፈሰስ ማድረግ ያለባቸው አምራች ለሆኑ ዘርፎች ነው፡፡ በተለይም እንደ ማኑፋክቸሪንግ፣ የግብርና ዘርፎች ማለትም የመስኖ እርሻ ላይ ነው፡፡ እዚህ ላይ አተኩሮ ቢሠራ ብዙ ማምረትና የዋጋ ንረቱን በቀላሉ መቆጣጠር ይቻላል፡፡ በዚያው ልክ አጠቃላይ የአገሪቱን ተቋማዊ ሥርዓትና ቁመና መፈተሽ ይገባል፡፡   

ሪፖርተር፡– በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አባላት፣ የፍትሕ ተቋማት በሌብነት ውስጥ መዘፈቃቸውን ተናግረው ነበር፡፡ ይህንን ንግግራቸውን እንደ ምክር ቤት እንዴት አያችሁት?

ዶ/ር መብራቱ፡- ይህ እንግዲህ ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን በግሌ ሁሉም ተቋማት በዚህ ውስጥ ይዘፈቃሉ ብዬ ባላስብም ብዙ ችግሮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ መንግሥት ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ነገር ግን እንደዚያም ሆኖ ተጠያቂው ራሱ መንግሥት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሁሉ እስኪፈጠር ድረስ የቁጥጥር ሥርዓቱ የት ነበር ብለን ጥያቄውን የምንመልሰው ወደ እነሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– እስኪ ስለእርስዎ የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ይንገሩን?

ዶ/ር መብራቱ፡- ፓርቲያችን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ ፓርቲው በዚህ ክልል የሚከሰቱ ችግሮችን አስመልክቶ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሲጮህ ነበር፡፡ በአካባቢው አሁንም መብራት የለም፣ ጉዞ በእጀባ ነው፡፡ ዛሬ በካማሺ ዞን ጦርነት አለ፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ካሉት ዞኖች እኛ በብዛት የምንንቀሳቀሰው በመተከልና በአሶሳ ዞኖች ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች እስካሁን ምርጫ አልተከናወነም፡፡ ያልተመረጠ መንግሥት ነው ያለው፡፡ ይህ እንግዲህ የሰላም ዕጦቱ የፈጠረው ችግር ነው፡፡ አካባቢው የህዳሴው ግድብ የሚገኝበት በመሆኑ፣ መንግሥት ለውጥ የሚለው ጉዳይ እዚያ አካባቢ እንዲገባ በተለያየ ጊዜ አበክረን ስንናገር ነበር፡፡ እንደ ፓርቲም ከመንግሥት የአብረን እንሥራ ጥያቄን ተቀብለን በክልል፣ በዞንና በወረዳም እስኪ የአቅማችንን አግዘን ለውጥ የሚመጣበትን መንገድ እንይ በሚል ገብተን አብረን እየሠራን ነው፡፡ ወደ 114 ባለሀብቶች ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ከልማት ባንክ ወስደው መጥፋታቸውን መረጃውን ያወጣነው እኛ እንደ ፓርቲ የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለን ከገባን በኋላ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ከቅር ጊዜ ወዲህ ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እስርና አፈና ተደጋግሞ ተስተውሏል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት እየወሰደ ባለው ዕርምጃ ሕገወጥ ናቸው ያላቸውን ተጠያቂ የማድረግ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር መብራቱ፡ማንም ሰው ጋዜጠኛ ስለሆነ መታሰር የለበትም፡፡ ነገር ግን የዴሞክራሲ ሥርዓታችን እጅግ ጠባብ በመሆኑና ማዕቀፉም ስፋት ስለሚጎድለው ሥርዓቱ ለዚህ ሲጋለጥ ይታያል፡፡ ነገር ግን ታዋቂ ሰዎችና ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ሊታሰሩ አይገባም ብዬ አምናለሁ፡፡ የፓርቲያችን አቋምም ይኼው ነው፡፡ ድርጊቱንም እናወግዘዋለን፡፡ በተቻለ መጠን ግን ማንም ሰው ከሕግ በታች በመሆኑ ካጠፋ በአገሪቱ ሕግ መሠረት መጠየቅ አለበት፡፡ እዚህ አገር ግን ብዙዎቻችን ለሕግ አንገዛም፡፡ ለምሳሌ ገዢው ፓርቲ ባለሥልጣን በመሆኑ ሕጉን እኔ ነኝ ያወጣሁት በማለት ሲጥሰው ይታያል፡፡ ራሱ ገዥው ፓርቲ ሕግ ካላከበረ ሌላው ሊያከብር አይችልም፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ሁሉም አበክሮ ቢሠራ ለውጦች ይኖራሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኞች ያለ ጥፋታቸው መታሰር የለባቸውም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ሆላንደር ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...