Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ለሌላ የዋጋ ንረት ሰበብ እንዳይሆን

ዓለም ከገጠማት ወቅታዊ ቀውስ አንፃር በርካታ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮት እየገጠማቸው ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት የእያንዳንዱ አገር ፈተና መሆን ከጀመረ ሰነባበተ፡፡ በኢኮኖሚ አቅማቸው አንቱ የተባሉት አገሮች ሳይቀሩ በዚሁ የዋጋ ንረት እየተፈተኑ ነው፡፡ በአንዳንዶች አገሮች አሁን እየተመዘበ ያለው የዋጋ ንረት በታሪካቸው አጋጥሟቸው የማያውቅ መሆኑም እየተዘገበ ነው፡፡ ከ40 እና ከ50 ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የተባለ የዋጋ ንረት ገጥሞናል ያሉ አገሮችም ችግራቸውን ሪፖርት እያደረጉ ነው፡፡  

ለምሳሌ በእንግሊዝ የተመዘገበው የዋጋ ንረት 9.1 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህ ከ40 ዓመታት በኋላ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ ሌሎች አገሮችም መጠኑ ይለያይ እንጂ ከፍተኛ ያሉትን የዋጋ ንረት እያጻፉ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም እንዲህ ያለው ዜና ተደጋግሞ የመነገሩ ዋነኛ ምክንያት የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ደግሞ የዋጋ ንረቱ የዓመታት ታሪክ ያለው ቢሆንም፣ ይህ ጦርነት ችግሩን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› አድርጎባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ለዋጋ ንረቱ መባስ በአገር ውስጥ የተፈጠሩ የፖለቲካ ቀውሶች፣ የግብይት ሥርዓቱ ብልሽትና ተያያዥ ችግሮች በአግባቡ መፍታት ሳይቻል የተከሰተው የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት ሁኔታዎችን አክብዷል፡፡ 

ይህ የዋጋ ግሽበት መንግሥትን ፈትኗል፡፡ ‹‹የቻልኩትን ያህል ብለፋም በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ተግባሮች ያገኘሁትን ውጤት በዋጋ ንረቱ ላይ ማስመዝገብ አልቻልኩም›› እስከማለት መድረሱ የችግሩን አሳሳቢነት በሚገባ ያመለክታል፡፡

እስካሁን የተወሰዱት ዕርምጃዎች የዋጋ ንረቱን አሁን ከሚታየው በላይ እንዳይሆን ዕገዛ ማድረጉን ቢያመላክትም፣ አሁንም የዋጋ ንረቱን ሊያብሱ የሚችሉ ተግዳሮቶች ከፊታችን እየመጡ ስለመሆኑ እየተመለከትን ነው፡፡ 

በተለይ ከቀናት በኋላ ይተገበራል ተብሎ የሚጠበቀው አዲስ የነዳጅ ሥርጭትና የዋጋ ተመን ጉዳይ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ ይህ ትግበራ የዋጋ ንረቱን በሚያባብሱ ችግሮች ላይ ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚለው ሥጋት እየተሰማ ነው፡፡ መንግሥት ከነዳጅ ድጎማ ለመውጣት የቀየሰው ይህ አሠራር በትክክል የታለመለትን ግብ ላይመታ ይችላል የሚለው ሥጋት የሚመነጨው ደግሞ በበርካታ ምክንያቶች ነው፡፡ አንዱ ምክንያት የታቀደው የነዳጅ ሥርጭትና ዋጋ ትግበራ ሁለት ዓይነት ሲሆኑ፣ ማለትም ድጎማ የሚደረግላቸውና ከድጎማ ውጪ የሚሆኑ በሚል ተከፍሎ የሚተገበር በመሆኑ ነው። ድጎማ የተደረገላቸው ተሽከርካሪዎች የሚሰጣቸውን ነዳጅ ባልተገባ መንገድ ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚል እምነት ብዙ ባለሙያዎች እያንፀባረቁ በመሆኑ አሠራሩ ጥብቅ ቁጥጥር የማይደረግበት ከሆነ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችላል፡፡ ከዚህ ቀደም የተወሰኑ ዘርፎችን ለመጥቀም ወይም ለማበረታታት ተብለው የተሰጡ ዕድሎች ምን ያህል ሕገወጥ ተግበራት እንደተፈጸሙባቸው ብዙ ምሳሌዎች ስላሉ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አሠራር ብርቱ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ አዲስ የነዳጅ ዕደላ አሠራር ተመሳሳይ ችግር እንደማይገጥመው እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እንዲያውም አሠራሩ ለሌብነት የተጋለጠ ከመሆኑ አንፃር ይህንን ሥጋት የሚያስቀር አሠራርና አደረጃጀት ካልተተገበረ ትልቅ የሌብነት በር የሚከፍት ብቻ ሳይሆን በብዙ ችግሮች ውስጥ ያለው የነዳጅ ሽያጭ እንዳለና የማከፋፈል ሥራ ከድጡ ወደ ማጡ ሊገባ ስለሚችል ብርቱ ጥንቃቄ ያሻዋል የሚለውን መልዕክት ደግሞ ደጋግሞ ማሳሰቡ ተገቢ ይሆናል፡፡ 

ሌላው የነዳጅ ድጎማ አይደረግላቸውም የተባሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ሊያሳድሩ የሚችሉት ተፅዕኖ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች የሚያሽከረክሩት መኪና የነዳጅ ወጪያቸው ከፍ ሲል እነሱም ይህንን ወጪ ማካካሳቸው አይቀርም፡፡ ይህ የነጋዴ ተፈጥሯዊ ባህሪይ ነው፡፡ የሚያሳዝነው ግን ይህ የእነሱ ማካካሻ የሚያርፈው ሸማቹ ላይ ነው፡፡ ነጋዴ ወጪውን ያሠላል፡፡ በቀጥታ ለንግድ ሥራው ለተጠቀመበትም ሆነ እሱ የሚያሽከረክረው መኪና የነዳጅ ወጪው ከጨመረ ጭማሪን አሜን ብሎ ይቀበላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ያው እንደፈረደብን ያንን ጭማሪ እኛው ላይ መልሶ የሚደረብ ከሆነ ድጎማው በቀረብን ብለን ብንፈራ አይፈረድብንም፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም የአገራችን ነጋዴ የዋጋ አጨማመር ዘግናኝ ነው፡፡ በአንድ ሌትር አምስት ብር ከጨመረበት በአገልግሎቱ ወይም በሽያጩ ላይ የሚጨምረው ዋጋ 100 ብር ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ያልተገባ ጭማሪ እንዳይኖር መንግሥት ብርቱ ሥራ ይጠብቀዋል ማለት ነው፡፡ 

ስለዚህ የአገራችንን የግብይት ሥርዓት ብልሽትና በየአጋጣሚው ዋጋ ለመጨመር ሰበብ የሚፈልገው ጥቂት የማይባለው ነጋዴ፣ ይህንን አሠራር አስቦ ዋጋ ቢጨምር እንዴት እንደሚጠየቅና ሊወሰድ የሚገባውም ዕርምጃ መታሰብ አለበት፡፡ አዲሱ አሠራር ሸማችን ሳይጎዳ የታለመለትን ዒላማ ሊመታ የሚችለውም አሠራሩን በተመለከተ በቃል እየተነገረ ያለውን በተግባር ሲቀየር ብቻ ነው፡፡ አሠራሩ ያለ እንከን እንዲተገበር ብንመኝም ለተጨማሪ የዋጋ ንረት ምክንያት እንዳይሆንም እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም አሠራሩ ለተጨማሪ ዋጋ ንረት ምክንያት እንዳይሆን የምንመኘው ደግሞ እስካሁን የተሸከምነው የዋጋ ንረት ራሱ ከምንችለው በላይ በመሆኑ በሌላ ሰበብ ጫናው እንዳይበረታብን ስለምንሻ ነው፡፡  

የመንግሥት የነዳጅ ድጎማን ደረጃ በደረጃ ለማስቀረት መወሰኑ ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሌ እየደጎመ ለመቀጠል የሚያስችለው አቅም እንደሌለውም ይታመናል፡፡ ነገር ግን ከችግሩ ለመውጣት የመረጠው አሠራር ሌላ ጫና የሚፈጥር ላለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ በተለይ፣ በተለይ ብዙ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በማስፈጸም አቅማቸው ደካማነት ደጋግመን የምንወቅሳቸው በመሆኑ፣ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ አተገባበር ላይ ይህንን ድጎማ የማስፈጸም አቅም የማይኖራቸው ከሆነ ደግሞ ችግሩን የበለጠ ሊያብሰው እንደሚችል ከወዲሁ መታወቅ አለበት፡፡ ስለዚህ የማስፈጸሚያ ሥልቱ ጨዋና ብቃት ያላቸው ተቆጣጣሪዎችን ይሻል፡፡ የማስፈጻም አቅም ብቻ ሳይሆን ከሌብነት የፀዱ የሥራ መሪዎች ተቆጣጣሪዎች ያስፈልጉታል፡፡ ለማንኛውም ለመንግሥት ደግመን ደጋግመን የምንለው፣ በብርቱ የምናሳስበው ነገር ቢኖር አሠራሩ በትክክል እንዲተገበር አሠራሩን ለማሳለጥ አቅሙን አጎልብቶ ሥራ ውስጥ ይግባ ነው፡፡  

የነዳጅ ጉዳይ እንደ ሌሎች ጉዳዮች የሚታይ አይደለም፡፡ ብዙ ነገሮችን ይነካካል በአነስተኛ ግድፈት ኢኮኖሚው ላይ ችግር ይፈጠራል፡፡ የዋጋ ንረቱን ሊያባብስ ይችላል፡፡ አንድ ችግር ቢፈጠር ወይም ነዳጅ ጨመረ በሚል የሚፈጠር ሌላ የዋጋ ንረት ሊከሰት ስለሚችል፣ በዚህ ጉዳይ የሚኖረው አሠራር በጥንቃቄ መያዝ አለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የዋጋ ንረቱ ቢባባስ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥትን የበለጠ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ አሠራሩን በአግባቡ መምራት ካልተቻለና ውጤት የማይታይበት ከሆነም በፍጥነት ሌላ መፍትሔ ማበጀትንም ማሰብ ብልህነት ነው፡፡ በአጠቃላይ ይህ አሠራር ግድ ሆኖ ከተጀመረ ለሌብነት ያለመጋለጡንና ተጨማሪ የዋጋ ንረት ላለመፍጠሩ እርግጠኛ በመሆን መሥራት እንዲህ ያሉ ችግሮች ከተፈጠሩም በአስቸኳይ ዕርምትና ዕርምጃ ለመውሰድ የሚችል ቆራጥ አመራር የሚጠይቅ ነውና ጉዳዩ ከወዲሁ ይታሰብበት፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት