Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየመንግሥት አገር አይደለም ወይ?

የመንግሥት አገር አይደለም ወይ?

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የመንግሥት አገር ማለት የማይታወቅ፣ ወይም ያልተለመደ፣ አለዚያም ጭራሽኑ የቀረ አባባል አይደለም፡፡ አዎ ሕዝብ ራሱን በራሱ በሚያስተዳድርበት፣ መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር በተገናኘበት፣ ሕዝብ ተወካዮቹን፣ ተወካዮቹ አስፈጻሚውን በሚመሠርትበት፣ በሚያደራጅበት፣ እንዲህም አድርጎ መግራትና መቆጣጠር በሚችልበት፣ ይህም ወግ በሆነበት አገር ወይም እንደዚያ እንሆናለን በሚባልበት፣ እየተባለ መከራ በሚያዩበት አገር የመንግሥት አገር ብሎ ነገር አጉልም፣ ኋላቀርም፣ ክፋተኛም ይባል ይሆናል፡፡ የመንግሥት አገር ማለት ግን በምልዓተ ሕዝቡ ውስጥ፣ ‹‹በሰፊው ሕዝብ›› ቋንቋ፣ ሕግና ሥርዓት ያለበት አገር ማለት ነው፡፡ እንዴት በመንግሥት አገር እንዲህ ይሆናል የሚባለውም፣ በግለሰብም ሆነ በአካባቢ፣ በአገር ደረጃ አንድ ያልተለመደ ነገር ሲፈጸም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የመንግሥት ያለህ የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

ዛሬ ብዙ የሚወራለት፣ ብዙ መነጋገሪያና ከተለያዩ ማዕዘኖችም አንገብጋቢ የሆነው ሕግ የማስከበር የመንግሥት ሥልጣንና ተግባር፣ እንዲሁም ግዳጅ፣ የአገር ሥርዓትንና የሕዝብ ደኅንነትን መጠበቅን፣ ወንጀል መከላከልንና መከታተልን፣ ለአደጋና ለጥቃት ተጋላጭ ለሆኑት ጥበቃ ማድረግና ጋሻ ከለላ መሆንን ያካትታሉ፡፡ መንግሥትና በየትኛውም ደረጃ በሚገኘው የአስተዳደር ዕርከኑ አማካይነት የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ፣ ሕዝብን ከየትኛውም ዓይነት ጥቃት የመጠበቅና የመከላከል ይህን ኃላፊነቱን በዝንጉነትም (በቸልተኝነት) ሆነ በሌላ ምክንያት ሳይወጣ ሲቀር ለሚደርሰው ጥቃት መንግሥት፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላትና ባለሥልጣኖቻቸው በኃላፊነት ይጠየቃሉ ማለት ድረስ የዘለቀና የሠለጠነ ወግና ልማድ አለ፡፡ ይህን በመሰለ በሠለጠነና መንግሥትነቱ የሕዝብ በሆነና በተሳካለት አገር ደግሞ አገራችንን እየደጋገመ ያስቸገረን፣ ማባሪያና መላ ያጣ የሰሞኑን የመሰለ የጊምቢ ዓይነት አደጋ ሲደርስ፣ አሁንም በሠለጠኑ አገሮች፣ ለሰው ልጅ ክብር በሚሰጥ አገር ሟቾችን ለማሰብ፣ የቋሚውንም ሐዘን ለመጋራት የሐዘን መድረክ ይዘጋጃል፣ የሐዘን ቀን ይወሰናል፣ አበባ ይቀመጣል፣ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ተደርጎ ይውለበለባል፣ ወዘተ፡፡ ከዚህ የወግ ማዕረግ ሥርዓት በተጨማሪ፣ የተጠያቂነት ጉዳይ ስለመኖር አለመኖሩ ይጣራል፣ ይመረመራል፡፡

- Advertisement -

ከወግ ያለፈ እንዲህ ያለ ሥርዓት ለመገንባት ትግል የተጀመረው ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ 2010 ዓ.ም. መልክ መያዝና ውጤት ማሳየት የጀመረው ለውጥና ሽግግር ከአምባገነንነት ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ብርቱ አደጋ እያጋጠመው፣ የጉሊሶን፣ የጎንደርን፣ የጋምቤላን፣ የጊምቢን የመሳሰሉ በአገርም፣ በዓለምም ፊት የሚያሳፍርና የሚያስፈራራ ሕመም እያጋጠመው ይገኛል፡፡ ለምን? በምን ምክንያት?

የዚህ ምክንያት እንደ መላ ዓለም፣ እንደ አኅጉር፣ እንደ ቀጣናና እንደ ሰው ማሰብን መተጋገዝን፣ እንዲሁም መያያዝን በሚጠይቀው በዚህ ግዳጅና በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደ አገር እንኳን ማሰብ በመቸገራችን ነው፡፡ የኤፌዴሪ ሕገ መንግሥት ራሱ በፌዴራልና በክልል መካከል ያለውን ሥልጣን ሲያከፋፍልና ሲያደላድል፣ ‹‹ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ ክልላዊ መስተዳደር ያዋቅራል፡፡ የሕግ የበላይነት የሠፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል፣ ይህን ሕገ መንግሥት ይጠብቃል፣ ይከላከላል›› ይላል፡፡ የአገራችን ችግር ግን ይህ ሕገ መንግሥቱ የሚያቋቁመው አካባቢያዊ የራስ በራስ አስተዳደር አይደለም፡፡ ክልላዊ አካባቢያዊ የራስ በራስ አስተዳደርን የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ልዕልና አድርጎ ከመረዳት ይልቅ የብሔርተኞች ጎጣዊ ይዞታ አድርገው የሚያስቡ፣ ከብሔርተኛ ቡድን አልፎ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መፍጠር መከራ የሆነባቸው፣ ለብሔርተኛ ቡድናዊ የጌትነት ጥማታቸው የብሔረሰቦችን መብት መሣሪያ ለማድረግ ሲሉ የብሔረሰቦችን መብት መረጋገጥ ከብሔር ፓርቲነት የማይነጣጠል አድርገው የሚያታልሉና የሚያደናግሩ፣ ጥላቻን እንኳን ማሸነፍ ያልቻሉና ያልተሳካላቸው ቡድኖች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ መመናቀርና መንገሥ በመቻላቸው ነው፡፡ ይህን አደጋና እነዚህን ብሔርተኞች የተቃረኑና የተቋቋሙ እየመሰላቸውም ደግሞ፣ ኢትዮጵያንና የግል መብትን ያጠበቁ ግን የኢትዮጵያን እውነታ መረዳት የከበዳቸው ቡድኖችም የ‹‹ብሔር መብት›› የሚባል ነገር የሸሸ ፕሮግራም ይዘው እንፋለማለን ይላሉ፡፡ አንዳንዶችም ‹‹የብሔር ሉዓላዊነት›› የሚባል ነገርን የመከቱ መስሏቸው ሉዓላዊነትን ግለሰባዊ አድርገው እስከ ማሰብና እስከ መሞገት ተስፈነጠሩ፡፡

በፖለቲካ ማደግና መገናኘት የተሳናቸው እነዚህ ሁለት ዓይነት የ‹‹አንድነት›› እና የብሔር ፖለቲከኞች በሚንገታገቱበት ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር መብትንና የአገር አንድነትን አስማምቶ የሁለቱን ጎራ የመስበር የምር ሙከራ ያደረገው፣ እያደረገም ያለው በእነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እየተመራ ከኢሕአዴግና ከአጋሮቹ ስብስብነት ወደ ብልፅግና ፓርቲነት የተቀየረው ቡድን ነው፣ ነበር፡፡ ወደ ወጥ ኅብረ ብሔራዊ አተያይ እየተደረገ ያለው ሽግግር ግን ገና አዲስ እንደመሆኑ ዥንጉርጉርነት ወደ አላላሰ ኅብራዊ እምነት የመድረሱ የባህርይ ለውጥ (ሜታ ሞርፈሲስ) ገና ጥሬና ብስል ነው፡፡ የዚህ ልውጠት ሥምረት ብዙ ቀሪና ደንበር ገተር፣ ብዙ ገለፈት መግፈፍ እየጠየቀበትም ነው፡፡

ምናልባትም ከዚህ በላይና የባሰ ነው፡፡ ዛሬ ስለኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ወይም ለምሳሌ ኦሕዴድ፣ ወይም ኦዴፓና አዴፓ ማለታችን ቀርቶ የኦሮሚያ ብልፅግና፣ የአማራ ብልፅግና ብንልም እያንዳንዱ ቅርንጫፍ ፓርቲዎች፣ በተለይም ሁለቱ የአንድ ብሔርን ጥቅም የማስጠበቅ ተቀዳሚ ዓላማ ያለው ፓርቲነት ከመሆን አልተላቀቁም፡፡ የወለጋው/ጊምቢ ዕልቂት የሐዘንተኛነትን ስሜት ሳይቀር (ሊናገሩት በሚያሳፍርና በሚቀፍ ሁኔታ) ከአንዱ ይልቅ የሌላው ያደረገው የወንዜ ልጅ፣ የብሔሬ፣ የፓርቲ ወገኔ ሳይሉ ማናቸውንም አድልኦ፣ በደልና ግፍ፣ እንዲሁም ጭፍጨፋ መቃወም ሥር ስላልያዘ ነው፡፡

ይህን የልውጠት ፈተና ከባድና ምናልባትም አዳጋች የሚያደርጉ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከ1983 ዓ.ም. የሕወሓት ኢሕአዴግ ድል ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካና አገዛዝ ላይ የነገሠው ክፍልፋይ ብሔርተኛነት የአንድ አገር ዜጎችን በብሔርሰብ ማንነታቸው ቤተኛና ባይተዋር፣ ባለቤትና ባዳ አድርጎ ከፍሎ ባይተዋር ባላቸው ላይ ልዩ ልዩ በደል ሲፈጽምና ሲያስፈጸም መኖሩ ትንሹ ትልቁም የሚያውቀውና አሁንም ያለ፣ እንዲያውም ተባብሶ የትግል መሣሪያም የሆነ እውነታ ነው፡፡ ክፍልፋይ ብሔርተኛነት የበደል መፍለቂያ ሊሆን የቻለውም የራሱን መገኛ ብሔር/ብሔረሰብ የእኔ ብሎ አቅርቦ ሌላውን ስለሚያርቅና መጠቃቀምን በብሔር ውስጥ አጥብቦ ንቃትና ተግባር ስለሚያደርግ፣ በዚህም መሠረት አድሎኛ ሕግ፣ ደንብና መመርያ እስከ ማውጣት ድረስ ስለማያፍር ነው፡፡ የእኔና የእኔ ያልሆነ፣ ባለአገርና ባላገር ያልሆነ (አገር የለሽ) ባለቤትና ባለቤት ያልሆነ ቤተኛና ባዳ (ባዕድ) ወዳጅና ጠላት ብሎ የፓርቲ አደረጃጀትንና የክፍለ አገሮችን አሸናሸን መራኝ ባለው የነጎደና ያበደ አገር፣ ‹‹…ራስን በራስ ማስተዳደርን ዓላማ ያደረገ… የሕግ የበላይነት የሠፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገነባል›› ማለት ዘበት ነው፡፡

ሀቁ ይህን ያህል በተግባርም በሰነድም ግጥጥ ብሎ እያለ ዛሬም ብሔርተኝነትን እንደ ሃይማኖት የያዙ ፖለቲከኞች የርዕዮተ ዓለማቸውን የአድልኦ ምንጭነት በማመን ፈንታ፣ በደል ሊደርስ የቻለው ዴሞክራሲ ባለመኖሩ ነው እያሉ ይሸመጥጣሉ፡፡ ዴሞክራሲ አልባነት ለዚህ ዓይነት በደል ምንጭ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት ወደ ደርግ ዘወር ብሎ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ባለቤት፣ ብሔርና መጤ ተብሎ ታምሷል ወይ ብሎ መጠየቅ ብቻ ይበቃል፡፡ ወደ ደርግም መሄድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ብሔርተኞቹ ዛሬም በራሳቸው ደጋፊዎችና በብሔርተኛ ቢጤዎቻቸው የሚካሄደውን አንጓላይነት፣ ማፈናቀልና ወርሮ ማጥቃት ለማስተዋልና ለመታገል መፍቀድ ነው፡፡ ከአንጀት እስኪመክን ሊታገሉት ከተነሱ ያለ ጥርጥር ራሳቸው ከሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ጋር መቃረናቸው አይቀርም፡፡ ርዕዮተ ዓለማዊ ሥሩን እስካልነኩት ድረስ ደግሞ ትግላቸው በአረም የሚመለስ ከመሆን አያልፍም፡፡

ቤተኛና ባይተዋር፣ ባለአገርና ባላገር ያልሆነ፣ ወዳጅና ጠላት ብሎ ዜጎችን የሚያቀርብና የሚያርቅ ብሔርተኝነት ከዴሞክራሲ ጋር ቢገናኝም በግልጽም በሥውርም ላዳላ እያለ ከዴሞክራሲ ጋር መጋጨቱ አይቀርም፣ ይጋጫልም፡፡ ዴሞክራሲ አድልኦን ለመታገልና ለመጠየቅ መድረክ ይሆናል እንጂ፣ በብሔርተኝነት ውስጥ ያለውን አድልኦኛ አመለካከት ነፍስ አይነቅልም፡፡ ሁለቱ አብረን እንኑር ካሉ ወይ ዴሞክራሲ ብሔርተኛ አድላዊነትን እያራወጠ ደብዛውን ያጠፋዋል፡፡ ወይ ብሔርተኛነት ዴሞክራሲን እንደ ቀበኛ በልቶ በቀፎው ያስቀረዋል፡፡ ወይም ብሔርተኛ አድልኦ የተወሰኑ አድልኦዎችን ሕጋዊ ለማድረግ ችሎ፣ ዴሞክራሲም ተቋማዊ ህልውና አግኝቶ አድልኦውን በወደዱና ባልወደዱ ኃይሎች ትንቅንቅ ምክንያት ከጊዜ ጊዜ የፖለቲካ ሰላም መታጣቱ አይቀርም፡፡ ብዙ የፖለቲካ ቡድኖች በብሔርተኝነት ውስጥ መንቦጫረቅን ሙጥኝ ያሉት፣ በአገራችን የተከመረው ልምድ ይህችን ያህል ግንዛቤ ለመጨበጥ አንሷቸው ነው? ወይስ አድልኦን በግልጽም በሥውር መልክ አቋቁመው ለመግዛት ስለሚፈልጉ?

ሁለተኛ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ጉልህ ሚና ባላቸው የአማራ፣ የኦሮሞና የትግራይ ልሂቃን ዘንድ ሥር የሰደደ የአስተሳሰብ መቦዝና ጠምዛዛነት መኖሩ ሁነኛ የኢትዮጵያ ቁርጠት ነው፡፡ በክፍለ አኅጉራዊና አኅጉር ገብ ዕይታ የታጀበ ኅብረ ብሔራዊ አዕምሮ ያለውን የአሁኑን ልውጠት የኦሮሞ ልሂቃን በዋናነት ይምሩት እንጂ፣ የኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ የብዝኃነት ካርታ የትኛውም ጥግ ድረስ ኦሮሟዊ መሠረጫጨት የተካሄደበት ኦሮሞነት የኢትዮጵያነት ሥዕል ዋና ወዘናና እርግብግቢት የሆነበት ታሪክ የተከናወነ እንደመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦችን አንድ ላይ ይዤና አስማምቼ እንደምን ኢትዮጵያን ላንሳት የሚለው ጉዳይ የኦሮሞ ልሂቃን ትርታ መሆን ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ኢትዮጵያነትና ኦሮሞነት የተላላሱበትን እውነታ ስተው፣ የኦሮሞን ነፃነት ያለ ኢትዮጵያ ለማግኘት የሚፈልጉ፣ ኦሮሞነት በገዳዊ ጎዳና ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ አገር ሠርቶ ሳለ፣ የኦሮሞ መሬት ከዚህ፣ እስከዚህ ነው፡፡ እነዚህ ሥፍራዎች የኦሮሞ ናቸው እያሉ የሚብከነከኑና የበቀልና የጥላቻ ልሂቃን መበርከታቸው ከየትኞቹም ብሔርተኞች በላይ መወቀሻቸው ነው፡፡

ታሪክ ያላላሰው በተለይም ኦሮሞነት ያላቀለመው ‹‹የጠራሁ ነኝ›› የሚል ብሔረሰብ በኢትዮጵያ የለም፡፡ በጥራት የለሽነትም ኦሮሞንና አማራነትን የሚያህል የለም፡፡ ዛሬ ባለ አማራነት ውስጥ የሸዋ፣ የጎጃም፣ የወሎም ሆነ የጎንደር አማራነት ውስጥ በአያቴ፣ በእናቴ፣ በአባቴ፣ እያለ ከሌላ ብሔረሰብ ጋር በተለይ ከኦሮሞ፣ ከአገውና ከትግሬ ጋር ትውልዱን የሚያጣቅስ ሰው ማግኘት ከባድ አይደለም፡፡ በሌላ አባባል አማራነት በብዙ መልኩ፣ ልዩ ልዩ ማኅበረሰባዊ ዝንቆች አማርኛ ተናጋሪ እየሆኑ የመምጣት ታሪካዊ ጉዞ ሆኖ ሳለ፣ የአማራነትን ታሪክ እስከ ጥንት፣ ከጥንትም እስከ ዘመነ አዳም የገነት ወንዞች ድረስ የሚያደርሱ ‹‹ልሂቃን›› ብቅ ብለዋል፡፡

ኢትዮጰያ ውስጥ የደራው ጎጆኛት ባለ ባላ ነው፡፡ የባላው አንድ መንትያ ማንነትን አኮማትሮ የብሔር/ብሔረሰብነት ተለዋጭ መጠሪያ አድርጎታል፡፡ ስለማንነት ከተወራ ስለብሔር/ብሔረሰብነት መወራቱ ሆኗል፡፡ ከዚሁ በመነሳትም ማንነትንና የማንነት አካባቢን አውቆ ለእምዬ አካባቢ ልማት መዋደቅ፣ የትም (በሩቅም በቅርብም) እየሠሩ ወደ እናት ምድር ማፍሰስ የሁሉም ጎጆኛነት ብሌን ሆኗል፡፡ በባላው ሌላ ጎን ደግሞ ብሔረሰቦችንና ክልሎችን እንደ ሉዓላዊ አድርጎ ማየት፣ በአስተደደር ክልል ያለ የተፈጥሮ ሀብትን (መሬትን፣ ማዕድናትና ውኃን) ሁሉ የክልል፣ ከክልልም ሌሎችን የማይጨምር የነባር ብሔር/ብሔረሰቦች የብቻ ሀብት አድርጎ ማሰብ አለ፡፡

እነዚህ ሁለት መንትያ አስተሳሰቦች፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የተወለዱበትንና እንጀራ ልጆች ያፈሩበትን የትኛውንም ሥፍራ አገሬ ብሎ መቁጠርን በጣጥሰዋል፡፡ በየአካባቢው ባለቤት ከሚባሉት ነባር ብሔረሰቦች ውጪ የሆኑ ማኅበረሰቦችንና ግለሰቦችን ያለቤታቸው፣ ያለአገራቸው የሚኖሩ ባይተዋሮች፣ ሁለተኛ ‹‹ዜጎች›› አድርጓል፡፡ ከዚያም አልፎ የማፈናቀልና የግጭት መነሻ ሆኗል፡፡ ከብሔረሰብ ቢጤኛነትና ከአካባቢ ልጅነት የዘለለው የአገር ልጅነት፣ የቅይጥ ዝርያነት፣ በረዥም ዘመን ማኅበራዊና ባህላዊ መስተጋብር ውስጥ የተገኙ የጋራ ገጽታዎችና ትስስሮች ድንግዝግዝ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በዛሬው የተሳሰረ ዓለም ውስጥ፣ ያውም በአፍሪካ ቀንድ ዕምብርት ውስጥ ቁርጥራጭ አገር መሆንን እንደ መብት ማየት በእሳትና በትርምስ ውስጥ መኖርን፣ ድህነትንና ጉልበት የለሽነትን እንደ መብት መቁጠር መሆኑ ተዘንግቷል፡፡ ሉዓላዊነት (በራስ ዕጣና ጉዞ ላይ ራስ ወሳኝ የመሆን ሥልጣን)፣ እንኳን በብሔር/ብሔረሰብ ደረጃ ይቅርና እንኳን በኢትዮጵያ ደረጃ ይቅርና፣ በእነ አሜሪካም ደረጃ በዓለማዊ መጠቃለል ከጊዜ ጊዜ ተቆነጣጥሮ የተመናመነ ነገር መሆኑ፣ ትምህርት በቀመሱ ሰዎች አካባቢ እንኳ ተራ ግንዛቤ አልሆነም፡፡

ሰላምና ተያይዞ የማደግ ዕድል ከእጃችን አፈትልኮ እንዳያመልጥ ከፈለግን ከአገር ልጅነት ትቅቅፍ ጋር የብሔር መብትንና መከባበርን ማጣጣም ግዳችን ነው፡፡ የትኛውንም የአገር ልጅ በእኩልነትና በወገንነት ማየት፣ የትም ሥፍራ ላይ አገሬ ብሎ በኩራት መኖርን፣ የየትኛውንም አካባቢ የልማት ጉዳት የእኔ ብሎ መቆርቆርን ማጎልበት አዘላለቃችንን በእጅጉ ይወስናል፡፡ ማጎልበት ሲባልም በአዳራሽና በጋዜጣ የመስበክ ጉዳይ ሳይሆን አመለካከቱን በተግባር ለመኖር የመቻል ነገር ነው፡፡ ይህን አመለካከት የምር ለመኖር ከፈለግን ደግሞ እስካሁን ያለውን የፓርቲ አደረጃጀት ከመከለስ አናመልጥም፡፡ ብዙ ማኅበረሰቦችን ባካተተ የአካባቢ አስተዳደር ላይ አንዱን ወይም ሌላውን ብሔረሰብ መሠረት አድርጎ የተደራጀ ፓርቲ ሥልጣን መያዝ፣ ከዚያም በፊት እንዲህ ያለ ፖለቲካ ሊጤን ይገባል ወይ? ብለህ መጠያየቅ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የየራስ ጠባብ ወገንን የመጥቀም ሩጫንና ንቁሪያን ለማዳከም ከተፈለገ፣ የአካባቢ ፓርቲዎች የየአካባቢያቸውን ሕዝብ በጥቅሉ መሠረት አድርገውና የፓርቲ በራቸውን ክፍት አድርገው መደራጀታቸው ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡ አገር አቀፍ (ፌዴራላዊ) ሥልጣንን በተመለከተም ብሔርተኛ ቡድኖች ግንባር በሚባል ከለላ ተወሽቀው በአንድ ጊዜ ሁለት ነገር (የሁሉንም ሕዝብ የጋራ ጥቅምና ጠባብ አካባቢያዊ ተልዕኮዎችን፣ የሚያስተናብሩበትና አንዱ ተልዕኮ ሌላውን ሊጎዳ የሚችልበት የሁለትዮሽ ሥራ መቀየር ይኖርበታል፡፡ ማለትም በፌዴራል ሥልጣን ላይ የመውጣት መብት ኅብረ ብሔራዊ ስም ከመለጠፍ ጋር ሳይሆን፣ በአግባቡ አገር አቀፍ ስብስብ ያለው ውህድ ፓርቲ ከመፍጠር ጋር መገጣጠም አለበት፡፡

ብልፅግና ፓርቲ ራሱ ይኼው ችግር አለበት፡፡ ብልፅግና ከዚህ ችግር ውስጥ ራሱን መንጥቆ እንዲያወጣ ለማድረግና ይህንኑም ለማገዝ አስቀድሞ ዋናውን ችግሩንና ፈተናውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አንዲት ነገር ብቻ እንመልከት፣ ኦነግ/ሸኔ ከየት መጣ? ዓብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግሥት የዴሞክራሲ ሽግግርን ከማስኬድ በላይ፣ አወለካካፊ ነገሮች እየተፈታተኑት ነው፡፡ ፈተናው የሴራ ወጥመዶችን እያመለጡና ከጊዜ ጊዜ ከሚዘረገፉ የግጭቶች፣ የጥፋትና የማፈናቀል ጣጣዎች ጋር ከመመናተልም አበሳ ባሻገር፣ ባለሁለት ቢላ የመነጠል ዕቅድም እየተላወሰ ኦነግ ሸኔ ሲደራጅ ዓይተናል፡፡ መስረከም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹ለውጡ እንዲሳካ በሰላም ለመታገል ነው የገባነው›› ብሎን የነበረው ዳውድ ኢብሳ፣ በዚያው የመስከረም ወር ውስጥ ከዋልታ ቴሌቪዥን ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ፣ ኦሮሞ ቅኝ ስለመያዙና የዳውድ ኦነግ ሲታገል የቆየው ለመነጠል ለ‹ኢንዲፐንደንስ› መሆኑን ነግሮናል፡፡ ዓላማው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 እና በአፈጻጸም ጎዳናዎቹ በኩል የሚፈልገውን ለማግኘት፣ በሰላምና በሕግ መንገድ ብቻ መሥራት ቢሆን አንድ ነገር ነበር፡፡ ዳውድ ኢብሳ በዋልታ ቴሌቪዥን ከነገረን በበለጠ፣ መስከረም 30 በአሜሪካ ድምፅ በኩል ከጠረፋማ አካባቢዎች ባሻገር በመሀል ኦሮሚያ አካባቢም ታጣቂ እንዳለው ነግሮናል፡፡ ትጥቅ ያለ መፍታት ጉዳይም ከዚህ በፊት ኦነግ ከደረሰበት ልምድ የመማር ነገር ስለመሆኑ ጠቁሞናል፡፡ በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች እዚህ አካባቢ ተኮሱ፣ እዚያ አካባቢ ገደሉ ከሚባለውና ከዳውድ ኢብሳ ‹‹እናጣራለን›› ባይነት ባሻገር፣ ትጥቅ እያስፈቱና ዝቅተኛ ሹም እየቀየሩና የአስተዳደር ሰንሰለት የመበጣጠስ (ነፃ መሬት የመፍጠር መሰል ነገር) በተወሰነ አካባቢ እየተጀማመረ ስለመሆኑም ሰማን፡፡

በአማረ አቀባበል በቦሌ በኩል ሰላምን አንግቦ ገብቶ፣ ዋል አደር ከተባለ በኋላ ትጥቅ የሚፈታው ነፃነት ሲገኝ ስለመሆኑ ለመናገርና የተጠቃቀሰውን ዓይነት ከትጥቅ ጋር የተያየዘ እንቅስቃሴ ለማካሄድ መድፈር ብዙ ሰዎችን ግራ አጋብቷል፡፡ የዳውድ ኦነግ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ፣ የፖለቲካችን ባለበት ረጋጭነትና የጥርነፋ በደል ያሸማመቱትን ድጋፍ ተማምኖና በዚህ ኃይል አማካይነት ግቡን የማሳካት ዕድል ስለመኖሩ ገምቶ ነው፡፡ አነጋገሩና መሬት ላይ የሚታየው ጢሳጢስ የሚነግረን እንዲያውም፣ የገዥው ግንባር ኅብረት ከላላበት (በሰሜን በኩል ምን ታመጣለህ ባይ መሰል ፍጥጫ ካለበት)፣ ፀጥታና ሰላም ማስከበር አበሳ ከሆነበትና ለውጡ የነባርና የአዲስ ገብ ፓርቲዎችን የርብርብ ቡልኮ ካልተጎናፀፈበት ከዛሬዋ የቋፍ ጊዜ የተሻለ ሁለት ቀዳዳዎችን የሚሰጥ ዕድል አያጋጥመኝም የሚል ታክቲከኛነትን ነው፡፡

የሥሌቱ የምናልባት መተጣጠፊያዎችም ብዙ ናቸው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ችግሮች በተወጠረበት ክፍተት መሣሪያ እያሾለኩና ተሰሚነትን እያባዙ ቶሎ ሥርን መዘረጋጋትና ትጥቅ ፍታ ለመባል የሚከብድ ኃይል መሆን፣ ለመውጋት ወይም ትጥቅ ለማስፈታት ቢሞከር ነውጥ አስነስቶ የሚያደርጉትን ማድረግ፣ አለሳልሰው አክብረው ከእነ ትጥቅ ካምፕ ግባ መባል ከመጣ በሥውር የሚቻለውን ያህል ታጣቂ ማኅበረሰቡ ውስጥ መበተንና ማድባት፣ ምርጫ መጥቶ የኦሮሚያ ምክር ቤትን 2/3 ወንበር ለመቆጣጠር የሚበቃ ስኬት ከተገኘ እሰየው፣ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚካሄድ የውሳኔ ሕዝብ መርሐ ግብር አስይዞ ኦሮሚያን እንደ ፍላጎት እያስተዳደሩና እየቃኙ ቆይቶ በ50 ሲደመር አንድ የድምፅ ብልጫ መገላገል፣ ወደ እዚህ የሚወስድ የ2/3 ድምፅ ከመነሻውም የማያስገኝ የመበለጥ አዝማሚያ ከገጠመ፣ በተለይም ለአሀዳዊ ሥርዓት ማስፈራሪያነት የተመቸ ፓርቲ የኦሮሞን ድምፅ ከተሻማ በኮረጆ ዘረፋ ተፈላጊውን ድምፅ ማሟላትን፣ ወይም ድምፅ ተዘረፈ ብሎ አመፅ ማካሄድን እንደ አዋጪነታቸው እያዩ መጠቀም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህልውና ላይ የተደቀኑ ተበታትኖ ወደ መተላላቅ መሄጃ መንገዶች እነዚህን የመሳሰሉ ሁሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ወደ አዘቅት የሚያንከባልሉ ጎዳናዎች በአጎዳዳቸው ብሔርተኛ ፓርቲነትንና ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲነትን እያዩ አያማርጡም፣ አያዳሉም፡፡

 ቅኝ ተገዥነትንና ተነጣይነትን የሚያቀነቅን ቡድን ከፍርፍር የማያልፍ ስንጣሪ ዝንባሌ ከመሆን አልፎ፣ ትርምስ ሊፈጥር የማይችልበት አገራዊ መግባባትና ዴሞክራሲ ገና ባልተቋቋመት ደረጃ እንዲገባ መፍቀድ ጀብደኝነት ነበር፡፡ ወይም አቋሙን እንዲቀይር የማግባባት ድርድር መካሄድ ነበረበት የሚል ትችት አሁኗ ሰዓት ላይ ተገልጦላቸው ሊወረወሩ የሚቃጡ ካሉ፣ ‹‹ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ›› የተሰኘውን አባባል እያስታወስን መለስ ብለው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማኅፀን ምን ያህል ድርቀት እንዳለ እንዲያጤኑ እንመክራቸዋለን፡፡ ይህን ያህል አርቆ አስተዋይነትን ፖለቲካችን አፍላቂ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ሽግግራችን በአበሳዎች ባልተተበተበ ነበር፡፡ የእነ ዓብይ የለውጥ ቡድን በሕዝብ ድጋፍ ለመጀቦን ብዙ ክንዋኔዎችን የማከታተል ሩጫ ሊጠመድ የቻለው፣ የኩርፈኛ ጎራዎች አስታርቂ ለመሆን የተገደደው፣ በሳል ምክር ሊንጨፍጨፍለት ያልቻለው፣ የወጣቱን ትኩስ አቅም ከጀርባ አሠልፎ ለመግራት እነ ታማኝ በየነና ጃዋር መሐመድን መጠጋት ያስፈለገው፣ ከሁሉም የተቃውሞ ጎራዎች በኩል ተፈልቅቆ የወጣና ህሊናን የረታ የለውጥ ፖለቲካ መሪነት ስለጎደለ ነበር፡፡ ለዴሞክራሲ ለውጡ የሳሱ የተቃዋሚ ሠፈር ኃይሎች የለውጥ ቡድኑን ጥሪ ሳይጠብቁ አጀበውት ዴሞክራሲያዊ አመለካከትንም ሆነ ሰላምንና ፀጥታን በማስፋፋት፣ እንዲሁም ችግሮችን ከርቀት እያዩ የሚበጁ ሐሳቦችን በማዋጣት ሊያግዙት ያልቻሉት ማን ከልክሏቸው? የኢትዮጵያ ሕዝቦች በብጥስጣሽና በከፋፋይ ጥያቄዎች መታመሳቸው፣ ለውጥ ከፈነጠቀም በኋላ የቀጠለው፣ ከዚያም ብሶ አዲሲና አሮጌ ሌቦችና በቀለኞች በ‹‹ብሔር/በአካባቢ መብትና ጥቅም›› እየነገዱ ቀውስ ማራባት የቀለላቸው፣ በሁለት ሠፈር ያሉት ተቃዋሚዎች ከጠባቂነት ባለመውጣታቸውና የሚፈይድ መላ ይዘው ሕዝብ ውስጥ የመሥራት ሙያ ስላላሳዩ ጭምር አይደለምን!? ከብዙ አቅጣጫ ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም›› እንደመባሉ ያ ቢሞከር ኖሮ የመነጠልን ፍላጎት በሕገ መንግሥታዊ መንገድ መጋተር እንኳ የማይቻልበት የፍርክስ ቀውስ ውስጥ አገሪቱ ትገባ እንደነበር፣ በአሁኑ ሰዓት እንኳ አለማጤን ሌላው የፖለቲካችን ቅርብ አዳሪነት መገለጫ ነው፡፡

የዳውድ ኦነግ የሚከተለው ኦሮጌ መስመር ዓይናችን ሥር አፈር ልሶ በወጣቶቻችን ውስጥ ማረፊያ ማግኘቱም የእኛው ፖለቲካ የመካንነት ገጽ ነው፡፡ የቤት ሥራችንን ሠርተን ቢሆን ኖሮማ፣ ከማይለወጥ ሃይማኖት የሚተካከል የፖለቲካ ልብ ወለድ እንዲህ ሊያንገላታን ይቅርና ርዝራዡም በታጣ ነበር፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አንድነት ወይም ሞት›› እና ‹‹ጠባብ ብሔርተኛ›› እየተባባሉ ማዶ ለማዶ በሚነቃቀፉ ጎራዎች ውስጥ ተቀርቅረን የቆየን የዴሞክራሲ ወገኖች፣ በ‹ብሔር ብሔረሰቦች መብት› ስምና በብሔርተኛ አደረጃጀት ዘይቤ የተዘረጋው ጥርነፋ፣ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ህሊናና ግንኙነት ላይ፣ ብሎም በትግላቸው ላይ ካደረሰው ጉዳት ትምህርት ወስደን፣ የጎራ ቀፏችንን ሰብረን አለመውጣታችንና አንድ ላይ የገጠመ ፋይዳ አለመስጠታችን በራሱ ድርቀታችንን ይመሰክራል፡፡ ትምህርት ወስዶ የመፈየድ አቅም ቢኖረንማ ኖሮ የዜግነት መብትና የብሔር መብት፣ የፖለቲካና የአደረጃጃት ጎራ የሌላቸው የማይጣሉ መብቶች እንደሆኑና ሁለቱም መከበር የሚያሻቸው፣ የዴሞክራሲ መቋቋም መሆኑን የማሳየትና በሕዝብ ህሊና ውስጥ የማስረፅ የቤት ሥራችንን መሥራት በተዋጣልን ነበር፡፡ ይህንን የቤት ሥራችንን ሠርተን ቢሆን ኖሮ፣ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀትና ኅብረ ብሔራዊ አከላለል የብሔር መብቶችን ከማረጋገጥ ጋር የሚጣሉ ባልመሰለና ፓርቲያዊ የብሔር አደረጃጀት በተመናመነ ነበር፡፡ ‹‹ሕዝቦች›› ከማለት ወጥተን ‹‹ሕዝብ››  እንበል በሚል ዓይነት ልጣጭ ‹‹መፍትሔ›› ላይ መጨነቅና ‹‹ያለው አወቃቀር ከተነካ የብሔር ማንነት ተጨፈለቀ ማለት ነው›› የሚል አጭበርባሪነትም፣ በማኅበራዊ የፖለቲካ ንቃታችን ውስጥ አስቂኝ ነገሮች በሆኑ ነበር፡፡

መብቶች መስዋዕት ሳይደረጉ ለተመጣጠነ ልማትና ለዴሞክራሲ ባህል መጎልበት የሚስማማ (የመሬት ቀረኝ ትንቅንቅን የሚያስቀር የእነ ራያና የወልቃይት ዓይነቱን ጉዳይም ‹‹ከሞቼ እገኛለሁ›› እልህ የሚገላግል፣ የሚጢጢና የግዙፍ ክልሎችን ግንጥል ጌጥ ያስወገደ)፣ የአንዱ አካባቢያዊ ሥልጣን ግድ በሌላው ሥር በማይገባበት አኳኋን አምስትና ስድስት ያህል ትልልቅ ራስ ገዝ የፌዴራል አባል ምድሮች ማዋቀር ከባድ ባልሆነ (ሐሳቡን ማቅረብ እንኳ ጫጫታ ይፈጥራል ተብሎ ባላስፈራ) ነበር፡፡ የቤት ሥራችን መወዘፍ ይህንን የመሳሰለውን የዕርማት ዕድል የማክበድ ጉዳት ብቻ አይደለም ያደረሰብን፡፡ በአሁኑ ሰዓት የለውጥ ጅምሩን ከቅልበሳ ማዳንና ተበታትኖ ከመፋጀት ማምለጥን ዋና ተግባር አድርጎ ደቅኖብናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ