Saturday, May 18, 2024

ለትግራይ ክልል የሚላከው የምግብ ድጋፍ ወደ በቂ ደረጃ መጠጋቱን የአውሮፓ ኅብረት አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ለትግራይ ክልል የሚላኩ አስፈላጊ ሰብዓዊ ድጋፎች አቅርቦት ላይ መሻሻሎች እንዳሉና የምግብ ድጋፍ አቅርቦቱም ለክልሉ ሕዝብ ወደሚያስፈልገው በቂ ደረጃ መጠጋቱን የአውሮፓ ኅብረት አስታወቀ፡፡

ወደ ክልሉ የሚሄዱት የምግብ ዕርዳታ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች መጨመራቸውን እንደተመለከቱ የኅብረቱ አደጋና ሥራ አመራር ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርችች ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን አብዛኛው የመንገድ ክልከላ እስካሁን መኖሩን፣ እንዲሁም አብዛኛው እቀባም መነሳት እንዳለበት በመጥቀስ፣ የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡

በተለይም የነዳጅ አቅርቦት እጥረት፣ ጥሬ ገንዘብ ያለመኖርና የሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን የገለጹ ሲሆን፣ ይህም እየቀረበ ያለውን የምግብ ዕርዳታ ተገቢውን ውጤት እንዳያመጣ እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

‹‹እየቀረበ ያለው የምግብ ዕርዳታ ከከተማ ርቀት ላይ ያሉ ሕዝቦች ጋ እንዳይደርስ የነዳጅ እጥረቱ ምክንያት ሆኗል፤›› ብለው፣ ‹‹አይደር ሆስፒታልን ስጎበኝ እንደተመለከትኩት ከሆነም ነዳጅ ለሕይወት አድን ሥራዎችና ጄኔሬተር ለማሠራት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ዓይቻለሁ፡፡ እሱ ላይ የተጣለው ዕገዳ መነሳት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀናት ጉብኝት ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ኮሚሽነሩ ትናንት ወደ ትግራይ ክልል ርዕሰ ከተማ መቀሌ ተጉዘው የነበረ ሲሆን፣ ከክልሉ ፕሬዚዳንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው እንደተመለሱ፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጋርም ተወያይተዋል፡፡

በትግራይ ክልል የጥሬ ገንዘብ መጥፋትም በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ኮሚሽነሩ የገለጹ ሲሆን፣ ይህም እጥረት የዓለም አቀፍ ድርጅቶችም የክልሉ ሠራተኞች ደመወዝ መክፈል እስካለመቻል ድረስ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡  

‹‹እንደ ኤሌክትሪክ ኃይልና ባንክ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት መመለስ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

አውሮፓ ኅብረት ጦርነቱ እንደተጀመረ አካባቢ ሦስት ጥያቄዎችን የጠየቀ ሲሆን፣ አንደኛው ግጭትን ማስቆም ሲሆን፣ ይህም የኤርትራን ወታደሮችን ከአገር ውስጥ ማስወጣትን ይጨምራል፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ያልተገደበ ሰብዓዊ ድጋፎችን መስጠትና የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ማስፈን ነበር፡፡ እነዚህ ጥያቄዎችን መመለስ ላይ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

ንግግሮችንና ስምምነቶችን በተመለከተ ኮሚሽነሩ ከፌዴራል መንግሥትና ከትግራይ ክልል አስተዳደር ጋር ያደረጉትን ውይይት በመጥቀስ ሁለቱ አካሎች ስምምነት ላይ በቅርቡ መድረስ ሊቻል እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በተያያዘም በድርቅ የተጎዱትን የሶማሌ ክልል አካባቢዎች በትናንትናው ዕለት መጎብኘታቸውን ኮሚሽነሩ በመግለጽ፣ በክልሉ ያዩት የድርቅ አደጋ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናትን፣ እንዲሁም ከብቶቻቸው የሞቱባቸው ቤተሰቦችን መመልከት ልብ የሚሰብር ነገር ነበር፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ ስለጉብኝታቸው ሲገልጹም፣ በኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት ከፍተኛ ደረጃ መድሱን አሳስበዋል፡፡

በአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ምክር ቤት አፍሪካን በተመለከተ በሰኞ ዕለት ውይይት ያደረገ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ጉዳይ ትልቁ አጀንዳ ነበር፡፡ የኅብረቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል በንግግራቸው፣ በአውሮፓ ኅብረትና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል ቢኖርም፣ ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ ግን በቂ ስላልሆነ ግንኙነታችን ጥንቃቄ የተሞላበት ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ የሚደረጉ ማንኛውም ግንኙነቶች በቅድመ ሁኔታዎችና ሰጥቶ በመቀበል ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፤›› ሲሉ ጆሴፍ ቦሬል ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -