Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባልታወቀ በሽታ ምክንያት ዶሮና እንቁላል ወደ ገበያ እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ሚኒስቴር በአንዳንድ አካባቢዎች ያልታወቀ የዶሮ በሽታ ተከስቷል በማለት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎችና እንቁላሎች ከቅርብም ሆነ ከሩቅ አካባቢዎች ወደ ገበያ እንዳይገቡ አገደ፡፡

ከተለያዩ የክልል ከተሞች ወደ አዲስ አበባ፣ ከውጭ አገር የሚገቡና ወደ ውጭ ሊላኩ የነበሩ ከ20 ሺሕ እስከ 40 ሺሕ የሚደርሱ የተፈለፈሉ ጫጩቶችና እንቁላሎች ገበያ ውስጥ እንዳገቡ ክልከላ ተደርጓል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ሰኔ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ለዶሮ አርቢዎችና ላኪ ድርጅቶች በጻፈው ደብዳቤ መሠረት ወደ አዲስ አበባ ሊገቡ የነበሩ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ የተፈለፈሉ ጫጩቶች፣ እንዲሁም የደረሱ እንቁላሎች ለገበያ እንዳይውሉ በመታገዳቸው የዶሮ ዕርባታ ድርጅቶች ከፍተኛ ኪሳራ እያጋጠማቸው መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር በደብዳቤው፣ ‹‹በተለያዩ ቦታዎች የዶሮ ሞት ክስተት እያጋጠመ በመሆኑ ችግሩ ተጣርቶ መፍትሔ እስከሚሰጥበት ድረስ የዶሮና የዶሮ ውጤቶች (የአንድ ቀን ጫጩትና የለማ እንቁላል) ገቢና ወጪ ላልተወሰነ ጊዜ ታግዷል፤›› ብሏል፡፡

በግብርና ሚኒስትር የኳረንቲን ኢምፖርት ኤክስፖርት ኢንስፔክሽንና ሰርተፊኬሽን ዳይሬክተር በሆኑት ወንድማአገኝ ደጀኔ (ዶ/ር) የተፈረመ ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ በዶሮ ዕርባታ የተሰማሩ ድርጅቶች የተጠቀሰውን ሕግ ተላልፈው ከተገኙ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ይጠቅሳል፡፡

ስለበሽታው መንስዔና አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው ወንድምአገኝ (ዶ/ር) ምላሽ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

ከግብርና ሚኒስቴር ክልከላው ከተላለፈበት ሰኔ 3 ቀን በኋላ በርካታ በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ ላይ ያሉ ድርጅቶች ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከአዲስ አበባ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኘው ቢሾፍቱ ከተማ ወደ አዲስ አበባና የተለያዩ ከተሞች የተፈለፈሉ ጫጩቶች፣ የዶሮ ሥጋና የደረሱ እንቁላሎችን የሚያከፋፍለው ቴዲ የዶሮ ዕርባታ ድርጅት ኪሳራ ካጋጠማቸው ድርጅቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡

‹‹ባሳለፍነው ቅዳሜ ብቻ 20 ሺሕ የሚደርሱ የተፈለፈሉ ዶሮዎችን አስወግጃለሁ፡፡ አሁን ደግሞ 50 ሺሕ እንቁላሎች አሉኝ፡፡ ዕገዳው በቶሎ ካልተነሳ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም፤›› ሲሉ የድርጅቱ ባለቤትና የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

‹‹እጄ ላይ የሚገኙትን እንቁላሎች ለተጠቃሚዎች መሸጥ ብችል አሁን በገበያው የተከሰተው እጥረት ሊቀረፍ የሚችል ሲሆን፣ ዕገዳው የሚቀጥል ከሆነ የእንቁላል ዋጋ እስከ 20 ብር ሊደርስ ይችላል፤›› ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ቴድሮስ ወደ ዶሮ ዕርባታ ባለፈው ዓርብ ከግብርና ሚኒስቴር በተላኩ ባለሙያዎች 20 ሺሕ የሚሆኑ የድርጅቱን ዶሮዎች ምርመራ የተደረገላቸው መሆኑን፣ በምርመራውም ምንም በሽታ እንዳልተገኘባቸው አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአንድ ወር በፊት በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቷል የተባለው ስሙ ያልታወቀው የዶሮ በሽታ ወረርሽኝ በአገር ላይ የመጣ ቢሆን ኖሮ፣ በድርጅታችን የሚገኙትን ዶሮዎች ሊገድል ይችል ነበር፤›› የሚሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ‹‹የተወሰነ አካባቢ ተከስቶ የጠፋ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሽታው ከየት እንደመጣና በምን ያህል ፍጥነት እንደሚስፋፋ ጥናት እያደረገ ያለው የግብርና ሚኒስቴር፣ የጥናቱን ውጤት ቶሎ እንዲያጠናቅቅ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የዶሮ አርቢዎች ማኅበር በበኩሉ ዕገዳው በርካታ በዶሮ ዕርባታ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችን ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ እየከተተ ስለሆነ፣ በግብርና ሚኒስቴር እየተከናወነ ያለው ጥናት እንዲፋጠን ጠይቋል፡፡

በዶሮ ሀብት ልማት እየተሳተፈ የሚገኘውና በርካታ የዶሮ አርቢዎችን በሥሩ የያዘው ኢትዮ ቺክን የዶሮ ዕርባታ ድርጅት፣ የግብርና ሚኒስቴር ዕገዳ ችግር እየፈጠረባቸው ስለሆነ ምርቶቹን ለማሠራጨት የሚያስችል ፈቃድ ለማግኘት ከሚመለከተው አካል ጋር ንግግር እያደረገ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በዶሮ ዕርባታው ውስጥ የሚገኙ የተፈለፈሉ ጫጩቶች በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ኢትዮ ቺክን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች