Sunday, May 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ያለው ሀብት ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአምስት ዓመታት በፊት በ33.1 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንደ አዲስ የተቋቋመው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን፣ የሚያስተዳድራቸው ቤቶች ዋጋ 71 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ2010 ዓ.ም. ሲያገኝ የነበረው ዓመታዊ ገቢ 300 ሚሊዮን ብር እንደነበር አስታውሶ፣ አሁን ግን ገቢው 2.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ይህንን ያስታወቀው፣ እሑድ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. 510 ቤቶችን ያያዘውን የገርጂ ዘመናዊ መኖሪያ መንደርና ከቀበና አደባባይ በ100 ሜትር ርቀት ወደ ጀርመን ኤምባሲ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘውን ባለአሥር ወለል የመኖሪያ ሕንፃ ባስመረቀበት ወቅት ነው፡፡

እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ በመግባቱ ‹‹የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች በቅጡ አያውቅም ነበር›› የተባለው ኮርፖሬሽኑ፣ አሁን ግን  መረጃዎችን ማደራጀቱን አስታውቋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዓመታት ባደረገው የቤቶች ቆጠራ የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች ቁጥር፣ ዓይነት፣ የሚገኙበትን አድራሻ፣ የተጠቃሚ ዓይነት፣ የገቢ መጠንና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎችን አደራጅቶ መያዙን ገልጿል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የሀብት መጠን ለማወቅ የቤቶች ዋጋ (Housing Valuation) በገለልተኛ አካል ተሠርቶ የኮርፖሬሽኑ የሀብት መጠን 71 ቢሊዮን ብር እንደሆነ መተመኑ ተጠቅሷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ3.06 ቢሊዮን ብር አስገንብቶ ያስመረቀው ዘመናዊ የገርጂ መኖሪያ መንደርም ገና ለነዋሪዎች ሳይተላለፍ ከተገነባበት ዋጋ በአሥር ቢሊዮን ብር ጨምሮ 13 ቢሊዮን ብር እንደተገመተ፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ካማል ተናግረዋል፡፡

ይሁንና የሀብት ግመታ መቼና በየትኛው አጥኚ እንደተከናወነ ግን አልተገለጸም፡፡ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች 20 ሺሕ ገደማ ቤቶችን የሚያስተዳድረው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በ2009 ዓ.ም. እንደ አዲስ ሲዋቀር፣ በዋነኛነት በሁለቱ ከተሞች ያለውን የቤት እጥረት መፍታት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ታስቦ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ አቁሞ የነበረውን አዳዲስ ቤቶች የመገንባት ሥራ እንዲያስቀጥልም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ከደቡብ ኮሪያ ያንግናም ዩኒቨርሲቲ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት አቶ ረሻድ፣ ኮርፖሬሽኑን በሥራ አስፈጻሚነት መምራት የጀመሩት ከ2010 ዓ.ም. አንስቶ ነው፡፡ በአቶ ረሻድ የሚመራው ኮርፖሬሽኑ ከ28 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ግንባታ አስጀምሮ በአዲስ አበባ በአምስት ሳይቶች ለመኖሪያና ለንግድ አገልግሎት ያስገነባቸውን ስምንት ብሎኮች ሰኔ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. አስመርቆ ነበር፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከአንድ ዓመት በኋላ ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ደግሞ በ18 ወራት ውስጥ ገንብቶ ያጠናቀቀውን የገርጂ የባለሥልጣናት መኖሪያ መንደር አስመርቋል፡፡ በሦስት ሔክታር መሬት ላይ የተገነባው ይህ የመኖሪያ መንደር ባለ 11 እና 12 ወለል 16 የአፓርትመንት ሕንፃዎችን የያዘ ሲሆን፣ ሁሉም ብሎኮች የተገነቡት የአልሙኒየም ፎርምወርክ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መሆኑ ተነግሯል፡፡

ሕንፃዎቹን በ18 ወራት ውስጥ ገንብቶ ያስረከበው ኦቪድ የተሰኘው የኮንስትራክሽ ኩባንያ ነው፡፡ የኮሪያው ኩምካንግ ካይንድ የአልሙኒየም ፎርም ወርክ ቴክኖሎጂውን ይዞ በመምጣትና ሥልጠና በመስጠት ሲሳተፍ፣ የህንዱ ፓሪን ሳህ አርክቴክትስ ደግሞ የሕንፃዎቹን ዲዛይን በማማከር አስተዋጽኦ አለው፡፡

በገርጂ የመኖሪያ መንደር የሚገኙ ቤቶች ከ150 እስከ 500 ካሬ ሜትር ስፋት ያላቸው ሲሆን፣ ባለ 500 ካሬ ሜትሮቹ ቤቶች ቅንጡ መኖሪያዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ቅንጡ የሆኑት ባለ 500 ካሬ ሜትር የስካይ ቪላ ዱፕሌክስ ቤቶች የሚገኙት በመንደሩ ውስጥ ባሉ ስድስት ሕንፃዎች ላይ ሲሆን፣ አንዱ ሕንፃ አምስት ቤቶችን ብቻ ይዟል፡፡ አንድ የስካይ ቪላ ዱፕሌክስ ቅንጡ መኖሪያ ቤት ሁለት ወለሎች አሉት፡፡

የገርጂው መኖሪያ መንደር 800 በላይ መኪና የሚይዝ የቤዝመንት መኪና ማቆሚያ፣ አዳራሽ፣ ጂምናዚየም፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ አምፊ ቴአትር፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የልጆች መጫዎቻ ቦታና ሌሎች አገልግሎቶች ይዟል፡፡

ቀበና አደባባይ አካባቢ የሚገኘው ባለ አሥር ወለል የመኖሪያ ሕንፃ 1,167 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን፣ ስፋታቸው እስከ ከ68 እስከ 140 ካሬ ሜትር የሚደርሱ ከባለ አንድ እስከ ባለ አራት መኝታ ክፍል ያላቸው መኖሪያ ቤቶችን የያዘ ነው።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ፣ ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች በ30 ሔክታር መሬት ላይ ቤቶችን ለመገንባት የአዋጭነት ጥናትና የዲዛይን ዝግጅት በማድረግ ገንዘብ እያፈላለገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ገንዘብ የማፈላለግ ሥራው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የገለጹት አቶ ረሻድ፣ በሁለቱ ከተሞች የሚጀመረው የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች