Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአማራ ክልል ሥራ ያልጀመሩ 169 ፕሮጀክቶች መሬት ተነጠቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአማራ ክልል በመጋቢት ወር በሰጠው የሁለት ወራት የጊዜ ገደብ ውስጥ ሥራ ያልጀመሩ 169 ፕሮጀክቶች መሬት ተነጠቀ፡፡

በክልሉ 937 ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የተሰጣቸውን መሬት ወደ ሥራ ሳያስገቡ ማስቀመጣቸውንና የክልሉ መንግሥት ሥራ ያልጀመሩ ኢንቨስተሮችን ለይቶ መሬት የማስመለስ ሥራውን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሚቀጥል፣ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ እድሪስ አብዱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መሬት የማስመለስ ሥራ ውስጥ የገባው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) መጋቢት 27 ቀን 2014 ዓ.ም. የክልሉን መሬት፣ ግብርና፣ ሰላምና ፀጥታ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮዎችን ጨምሮ ለሌሎች መሥሪያ ቤቶች የጻፉትን ደብዳቤ ተከትሎ ነው፡፡ ይልቃል (ዶ/ር) ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ባደረጉ ማግሥት በጻፉት በዚህ ደብዳቤ አምስት ትዕዛዞችን ያስተላለፉ ሲሆን፣ ከትዕዛዞቹ ውስጥ ቀዳሚው ‹‹ሥራ ያልጀመሩት የማይሠሩ መሆናቸው ተረጋግጦ ፕሮጀክቶችን በመረከብ መሬቱ በሕጉ መሠረት ለመንግሥት ገቢ እንዲደረግ፤›› የሚለው ነው፡፡ ፕሮጀክቶቹ ሥራ የማይጀምሩ መሆኑን ለማረጋገጥም የሁለት ወራት ጊዜ ተሰጥቶ ነበር፡፡

በዚህ ትዕዛዝ መሠረት በየተዋረዱ ያሉ የኢንቨስትመንት ቢሮዎችና የሚመለከታቸው አካላት ፕሮጀክቶችን የመገምገምና ሥራ የማስጀመር እንቅስቃሴ ማከናወናቸውን የሚገልጹት አቶ እድሪስ፣ በኃይል ዕጦት ቆመው የነበሩ ከ50 በላይ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ማስገባት መቻሉን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ የማሽን ተከላ ካከናወኑ በኋላ በተለያዩ ችግሮች ሥራ ላቆሙ ኢንቨስተሮች ድጋፍ ቢደረግም፣ እንደ ሲሚንቶ ያሉ ግብዓቶችና የውጭ ምንዛሪ እጥረት አሁንም ችግሮች መሆናቸውን አስረድትዋል፡፡

ዕገዛ ቢደረግላቸውም በሁለት ወራት ውስጥ እንቅስቃሴ ማሳየት ባልቻሉ ኢንቨስተሮች ላይ ደግሞ፣ ከማስጠንቀቂያ አንስቶ መሬት የማስመለስ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን አቶ እድሪስ ተናግረዋል፡፡ ኃላፊው የተሰጣቸውን መሬት ስለነጠቃቸው ኢንቨስተሮች ሲናገሩ፣ ‹‹ከዚህ ቀደም በየደረጃው ማስጠንቀቂያ እየተሰጣቸው ቆይተው መሥራት እንደማይችሉ በአመራሮች ተረጋግጦ 169 ፕሮጀክቶች ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ አቶ እድሪስ ገለጻ፣ መሬታቸውን የተነጠቁት ባለሀብቶች የክልሉ 28 ኢንዱስትሪ መንደሮች በሚገኙባቸው 13 ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ ናቸው፡፡ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ አብዛኞቹ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሰማራት መሬት የተረከቡ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ ብዙዎቹ መሬቱን አጥረው ተቀምጠው የነበሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ አክለውም ‹መሬቱን አየር በአየር ለመሸጥ ያስቀመጡ ናቸው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል (ዶ/ር) በመጋቢት ወር ከክልሉ ባለሀብቶች ጋር ባደረጉት ውይይት 937 ባለሀብቶች ለኢንቨስትመንት የተሰጣቸውን መሬት አጥረው መቀመጣቸውን፣ በዚሁ ሁኔታ ከአሥር እስከ 15 ዓመት የቆዩ ኢንቨስተሮች መኖራቸው ተገልጾ ነበር፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉትን ትዕዛዝ ተከትሎ በዞን፣ በወረዳና በከተማ ደረጃ ያሉ የኢንቨስትመንት ቢሮዎች መሬቶቹ ለምን ታጥረው እንደተቀመጡ በሁለት ወራት ውስጥ አጣርተው ዕገዛ እንዲያደርጉ ወይም ዕርምጃ እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

ይልቃል (ዶ/ር) ባስተላለፉት ትዕዛዝ ፕሮጀክት ተለይቶ መሬት ከተሰጣቸው በኋላ በሕግ ካልተወሰነ በቀር፣ ወደ ሌላ የኢንቨስትመንት ዘርፍ መቀየርም ተከልክሏል፡፡ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመት ቢሮ እንደሚያስረዳው ክልከላው የተደረገው ባለሀብቶች ትልልቅ ኢንቨስትመንቶችን ይዘው በመቅረብ መሬትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ካገኙ በኋላ፣ ፕሮጀክቱን ወደ አነስተኛ የኢንቨስትመንት ሥራ የመቀየር አዝማሚያ በመታየቱ ነው፡፡ በተጨማሪም ሥራ ባለመጀመራቸው ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ሲል ዘርፍ ለመቀየር በሒደት ላይ መሆናቸውን እንደ ምክንያት እያቀረቡ መሆናቸውም ለዚህ ትዕዛዝ በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

ካሉት ዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በሰባቱ ጦርነት የተደረገበት የአማራ ክልል፣ በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ ባደረገው ጥናት ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት መድረሱን አስታውቆ ነበር፡፡ የክልሉ መንግሥት አሁን ኢንቨስተሮችን በተመለከተ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ የማነቃቃት ዕርምጃ አካል መሆኑን፣ ሥራ አጥነትን መቀነስና በምርት እጥረት የመጣውን የኑሮ ውድነት መቅረፍ ዓላማዎቹ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊው አቶ እድሪስ ክልሉ ሥራ ባልተሠራባቸው መሬቶች ላይ አዲስ ባለሀብቶችን ማሰማራት እንደሚፈልግ ገልጸው፣ ከተነጠቁት 169 መሬቶች ውስጥ ለባለሀብቶች የተላለፉ እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ኢንቨስተሮች መኖራቸውን በመጥቀስም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ መሬት የማስመለስ ሥራው እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

በአማራ ክልል ውስጥ 6,500 ገደማ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ ሰባት በመቶ የሚሆኑት ብቻ በካፒታል መጠናቸውንና በሰው ኃይል ቅጥራቸው ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ ይመደባሉ፡፡ 73 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ዝቅተኛ አምራች ኢንዱስትሪ የሚመደቡ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች