Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከመጪው ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች በብቃት ምዘና እንዲያልፉ ሊደረግ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሙያ ደረጃቸውን ለማሳደግና የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት ለማግኘት የሚፈልጉ ማንኛቸውም ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች፣ ከመጪው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት በሚያዘጋጀው የብቃት ምዘናና ማረረጋገጫ ማለፍ እንደሚኖርባቸው ታወቀ፡፡

በአጠቃላይ ጀማሪዎችን ጨምሮ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ሦስት ደረጃ ያለው የሙያ ፈቃድ የሚያወጡ ሲሆን፣ ይህንንም የሚሰጠው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ቁጥጥር ባለሥልጣን ሲሆን፣ ባለሙያዎቹ በሚያቀርቡት የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ደብዳቤ ላይ ብቻ መሠረት ያደረገ ነበር። ጀማሪ ባለሙያዎች ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቁ፣ የተመራቂ መሐንዲስነት የምስክር ወረቀት ወዲያው የሚያገኙ ሲሆን፣ ከዚያም በአራትና በስምንት ዓመታት የከፍተኛ ባለሙያነትን ሰቲፊኬት ከባለሥልጣኑ ያገኛሉ ተብሏል፡፡

ይህ መመርያ ተግባራዊ ሲደረግ ጀማሪ ባለሙያዎቹ በዩኒቨርሲቲዎቻቸው መውጫ ፈተና ተፈትነው የሚወጡ ከሆነ፣ የብቃት ምዘናና ማረረጋገጫ መውሰድ ላይጠበቅባቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን በየአራት ዓመቱ ከባለሥልጣኑ ለሚወስዱት የምስክር ወረቀት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሚሰጠውን መመዘኛ መውሰድ እንደሚገደዱ፣ በኢንስቲትዩቱ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ባለሙያዎች ምዘና ሥርዓት ዝርጋታ ዳይሬክተር ቅድስት ማሞ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

‹‹ይህ መመርያ እንደፀደቀ በመጪው የመጀመርያ ግማሽ ዓመት ሲስተም እንዲዘረጋ ይደረግና በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ግን ተግባራዊ ይሆናል፤›› ሲሉ ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

ባለሙያዎቹ አዲስ ለሚያወጡትና ለሚያሳድጉት የምስክር ወረቀት ደረጃ ብቻ ለምዘና መቅረብ ሲጠበቅባቸው፣ ያላቸውን ለማሳደስ ግን በምዘናው ማለፍ አይጠበቅባቸውም ብለዋል፡፡  

ይህንን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ጥናቶችን ሲያካሂድ ቆይቶ መመርያ አርቅቋል፡፡ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትንም አስተያየት እንዲሰጡበት በማድረግ ላይ ነው። ኢንስቲትዩቱ የብቃት ምዘናውን ሲያከናውን፣ ባለሥልጣኑ ደግሞ በዚህ ያለፉትን ባለሙያዎች የማረጋገጫ ምስክር ወረቀት የመስጠት ኃላፊነት ይወስዳል ተብሏል፡፡  

በዲፕሎማና ከዚያ በታች ላሉ ባለሙያ ተመራቂዎች ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ እንደነበረው፣ የሙያ ማረጋገጫ ምዘናዎች (በተለምዶ ሲኦሲ እንደሚባለው) በዲግሪና ከዚያ በላይ ላሉ ተመራቂ ባለሙያዎች ከውስን የትምህርት ዓይነት የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተናዎች በስተቀር የሚካሄድ አልነበረም፡፡

እንደ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ታምራት ሙሉ (ኢንጂነር) ገለጻ፣ ይህ ምዘና ያስፈለገው ባለሙያዎቹ በሙያው ላይ መቆየታቸውንና የሙያ ምስክር ወረቀት ሲወስዱ ብቃታቸውን ለማወቅ እንዲረዳ ነው። ‹‹ምናልባት ባለሙያው ምሕንድስናውን ትቶ ነጋዴም ሌላም ቢሆንስ?›› በማለት የባለሙያዎቹን ሙያ ብቃት መመዘን አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡

‹‹የሥራ ልምድ ደብዳቤ ብቻ ማምጣት ብቃትን የሚለካ ስላልሆነ፣ በዚህ አተገባበር ተግባርንም እንለካለን፤›› ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኮንስትራክሽን ሙያ በአገሪቱ ውስጥ ከከፍተኛ ሥራ ቀጣሪ ሙያዎች ውስጥ አንደኛው ሲሆን፣ ይህም የአጠቃላይ ተቀጣሪ ሠራተኞችን አምስት በመቶ እንደሚሆን ይገመታል። ዘርፉ የአገሪቱን አንድ አምስተኛ ጥቅል ዓመታዊ  ምርት ይይዛል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች