Monday, May 27, 2024

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡም ተባለ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ማክሰኞ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በወሳኝና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡም ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ተናገሩ፡፡

የፓርላማውን ውሎ በሚመለከት ሐሳባቸውን ያጋሩ ፖለቲከኞችና የሕግ ባለሙያዎች በምክር ቤቱ አባላት ከተለመደው በተሻለ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ቢቀርቡም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን አንዳንዶቹን አውቀውም ይሁን ረስተው ዘለዋቸዋል ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ተገቢና ብዙዎችን የሚያስማማ በርካታ ሚዛን ደፊ ሐሳብ ማንሳታቸውን በበጎ ጎኑ ያወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ሊመለስ ሲገባው ተድበስብሶ አለፈ ያሉትን ሐሳብ አንስተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ራሔል ባፌ (ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ለተጠየቁ ጥያቄዎች በቀጥታ መልስ መስጠት ላይ ብቻ ያተኮረ ቢሆን ኖሮ፣ ሕዝቡ የተሻለ ውጤት ያገኝበት ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው አገር በቀጥታ የሚከታተለው ውይይት እንደ መሆኑ መጠን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው በቀጥታ መመለስ ላይ ቢያተኩሩ፣ የምክር ቤቱን ውሎ የበለጠ የተሳካ ያደርገዋል፤›› ሲሉ ራሔል (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ብሔራዊ ምክክሩን አስመልክቶም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋናነት ሒደቱ በምን አግባብ እየሄደ እንደሆነ የበለጠ ግልጽ በሆነ መንገድ ቢያብራሩ ምርጫቸው እንደነበር ፖለቲከኛዋ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹የብሔር ማንነቶችና ብሔራዊ ማንነቶችን አስታርቆ መሄድ፣  እንዲሁም የጋራ ታሪክና ትውስታ መፍጠር በሚቻልበትና በአገራዊ ምክክሩ እንዴት አካታች በሆነ መንገድ መምከር እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በበለጠ በግልጽ ማስረዳት መቻል ነበረባቸው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ውስጥ የትግራይ ተወላጅም ባይኖር የዚያ አካባቢና የዚያ ክልል ሕዝብ ጉዳይን የራስ ጉዳይ በማድረግ ማብራሪያ የሚፈልጉ ወሳኝ ነጥቦችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማንሳት ይቻል እንደነበር ያመለከቱት ራሔል (ዶ/ር)፣ ከዚያ ውጪ ግን አባላቱ ጠንከር ያሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲያቸው ኢዜማን ወክለው እንደማይናገሩ ያሳሰቡት መምህርና ፖለቲከኛ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ከፓርላማ አባላት የቀረቡ ጥያቄዎችን ‹‹አንዳንዶቹ ያለቦታቸው የቀረቡና የወረዱ፣ ሌሎቹ ደግሞ ተገቢ የሆኑ›› ጥያቄዎች ሆነው እንዳገኟቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ፓርላማ ውስጥ የተወሰነ ማኅበረሰብን ወክለህ ብትቀመጥም፣ ለአገር መሪ የምታቀርበው ጥያቄ ግን አገራዊ ቅኝት ያለው ቢሆን የተሻለ ነው፤›› ሲሉ ጥቂት ጥያቄዎች የጎደላቸውን ነገር አስረድተዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ በሚመለከት ደግሞ በጣፋጭ አንደበትና ቋንቋ ያስቀመጡት ብዙ ነጥብ መኖሩን በማስመር፣ ‹‹አንድ ቦታ ላይ ዳኞችና ሕግ አስከባሪዎችን ጭምር ሌቦች አሉ›› በማለት ጭምር ደፋር ንግግር ማድረጋቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሌቦች ባሏቸው አካላት ላይ ዕርምጃ ይወስዳሉ የሚለውን ብዙዎች እንደሚጠራጠሩት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚናገሩትን ሁሉ የማይፈጽሙ የሚሉና የሚናገሩት የማይጥማቸው ሰዎች እየበዙ መሆናቸውን  ያመለከቱት አቶ አበበ፣ በፓርላማው የሰጡትን ቃልም በተጨባጭ ወደ መሬት አያወርዱትም የሚል ሥጋት እንዳላቸው አክለዋል፡፡

‹‹በሁለት ወራት 1,000 የኦነግ ሸኔ አባላት ተገድለዋል ብሎ ሪፖርት ማቅረቡ አግባብነት የሌለው ነው፤›› ያሉት አቶ አበበ፣ ሕወሓት ተዳክሞና በራሱ ችግር ውስጥ ተዘፍቆ ሳለ፣ ‹‹የኦነግ ሸኔ ደጋፊ ሕወሓት ነው ብሎ ከመክሰስ ይልቅ፣ በኦሮሚያ እንደ ልብ እንዲንቀሳቀስ የፈቀደውን አካል መጠየቅ›› ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ሰላምና ድርድር ማድረጉ ተገቢነት ያለው መሆኑን የጠቀሱት አቶ አበበ፣ ‹‹ከሕዝብ የምንሰውረው ነገር የለም ብለው በፓርላማው ፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ቃል መግባታቸው፣ ጥሩና በቀጣይ ቀናት ተጨባጭነቱ በተግባር የሚፈተን፤›› መሆኑን አስምረውበታል፡፡

‹‹ሙስናው እንዳንገፈገፋቸው መናገራቸው ተገቢ ነው፡፡ ሕግ መከበር አለበት ብለው ያስቀመጡትም ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ጭምር ሰዎች ከሕግ ውጪ እየታፈኑ ነው፤›› በማለትም ከትናንት በስቲያ ታፍኖ ተወሰደ ስላሉት መምህር የሥራ ባልደረባቸውን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ ሽግግርና ለውጥን በሚመለከት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሽግግሩ እስከ ምርጫ እንጂ አሁን ያለነው በአምስት ዓመት የምርጫ ኮንትራት ላይ ነው፤›› ማለታቸው አግባብነት የሌለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‹‹ምርጫውን ገና በካርድ ዕደላ ጨርሰውት፣ በተጭበረበረ ሁኔታና የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ አመቻችተው እያካሄዱትም የአገር ህልውናን ለማዳን ሲባል እንተዋቸው/እንለፋቸው ስንል ነበር፡፡ ሕወሓት የህልውና አደጋ ደቀነ ብለን ምርጫውን ወደ ጎን ብለን ከብልፅግና እኩል ዘምተናል፣ የምንችለውን አድርገናል፡፡ ይህን ሁሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አድርገው የታለፈ ምርጫን መቶ በመቶ ሕዝብ መርጦኛልና እስከ አምስት ዓመት እንደፈለግኩ እሆናለሁ መባሉ ጥሩ አይደለም፤›› በማለት አቶ አበበ ተችተዋል፡፡ ‹‹አምስት ዓመት ሩቅ አይደለምና ደረት መንፋቱን ትተን በብሔራዊ ምክክሩ የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት በአግባቡ መወያየቱ ይበጀናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አብረሃም ጌጡ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በዋናነት ማጠንጠኛው ሕግን ማስከበር ላይ ነው ይላሉ፡፡ ሕግን ማስከበር፣ በሕግ መመራትንና የሕግ የበላይነትን ፓርቲያቸው እንደሚደግፍ የተናገሩት አቶ አብረሃም፣ ‹‹ነገር ግን ሕግን ተገን አድርጎ የፖለቲካ ሥልጣንና ኃይልን ያላግባብ መጠቀም ነው የምናየው፤›› በማለት ተችተዋል፡፡ ‹‹በአገሪቱ አሁን ላይ ካለፉ ሥርዓቶች ተምሮ በሕግና በሕግ አግባብ አገር ለመምራት የሚያስችል የፖለቲካ ሥራ አልተሠራም፤›› ሲሉም አቶ አብረሃም ተናግረዋል፡፡  

‹‹መንግሥት ሕግን ተጠቅሞ የሚፈልጋቸውን አይዞህ ማለት የማይፈልጋቸውን ግን አንገት ማስደፋትና ማሳደድ ነው የተያያዘው፤›› ሲሉ የተቹት አቶ አብረሃም፣ ለሕግ ማስከበር ዘመቻው የክልሉ መንግሥት ተጠያቂ ነው መባሉን እንደማይቀበሉ ተቃውመዋል፡፡ ‹‹አማራ ክልል ብቻ አይደለም አዲስ አበባና ሌሎች ክልሎች ውስጥም እኮ ሰዎች ሕግን ባልተከተለ መንገድ እየታፈኑ ነው፤›› ሲሉም ተከራክረዋል፡፡ ‹‹ክልሎች ለሚወስዱት አግባብነት ለሌለው ዕርምጃም ቢሆን ፌዴራል መንግሥቱ ራሱን ከተጠያቂነት ማውጣት አይችልም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የሦስት ዓመት ሕፃን ለታፈነበት ጥፋት ተጠያቂነትን መሸሽ አይቻልም፤›› የሚሉት አቶ አብረሃም፣ ነገሮችን አድበስብሶ ከማለፍ በዘለለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጥጋቢ መልስ አልሰጡም ይላሉ፡፡

‹‹በአማራ ክልል ለተፈጠረው ሕገወጥ ዕርምጃ የተሰጠው መልስም ቢሆን የአዲስ አበባን ጉዳይ በተመለከተ፣ እንዲሁም በብሔር ፖለቲካ ላይ ለተነሱ ነጥቦች የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ከእነ ችግሮቿ እንደምትቀጥል የሚያመላክት ነው፤›› በማለት አቶ አብረሃም የፓርላማው ውሎ አጥጋቢ መልስ ያልተገኘበት ነው ያሉበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

ስለፓርላማው ውሎ ጥቅል ምልከታቸውን ያጋሩት የሕግ ባለሙያው አቶ አንዷለም በዕውቀቱ በበኩላቸው፣ የፓርላማ አባላቱ ጥሩ ጠያቂ ቢሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን በተለየ ሁኔታ የራሳቸውን ዕሳቤ ማስተማርና ማጥመቅ ላይ ያተኮሩበት ሁኔታ እንዳጋደለባቸው ተናግረዋል፡፡

ያም ቢሆን ግን ሽግግርን በተመለከተ የሽግግር ጊዜ ማለፉንና በምርጫ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ዓብይ (ዶ/ር) መናገራቸው ጥፋት ሆኖ እንዳላገኙት አቶ አንዷለም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሆኖም ከ48 ሰዓታት በፊት ለደረሳቸው ጥያቄ ላስተምራቸው ብለው ተዘጋጅተው የመጡ ይመስላል፤›› ሲሉ ስለስብሰበው ያክላሉ፡፡

የሕግ ማስከበሩን ጉዳይ በተመለከተ፣ ‹‹በየከተማው ጠብመንጃ ይዞ ሕዝብን ማሸበርም ሆነ በጋዜጠኝነት ስም ፖለቲካ ማራመድ ሕገወጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ጥፋት የለውም፤›› ይላሉ አቶ አንዷለም፡፡ እሳቸው በግላቸው ብዙ የፋኖ አባላትን በአካል እንደሚያውቁ የተናገሩት አቶ አንዷለም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአቶ ክርስቲያን ታደለ አንዳንድ ፋኖዎችን በማግባባት ከጥፋት ለመመለስ ሞክረው አልተሳካለዎትም እንዳሏቸው ሁሉ፣ እሳቸውም በግል ለማግባባት ሞክረው ከጥፋት አንመለስም ያሉ አንዳንድ ፋኖዎች እንዳጋጠሟቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹ከጥፋት አንመለስም ያሉትንና በሕገወጥ መንገዳችን እንቀጥላለን ብለው ከተማ ሲያተራምሱ በቆዩና በፋኖ ስም በሚነግዱ ኃይሎች ላይ መንግሥት ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰዱ የሚደገፍ እንጂ የሚወገዝ አለመሆኑን›› በማከልም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹በዚህ በኩል አጥጋቢ መልስ ሰጥተዋል›› ብለዋል፡፡ በጋዜጠኝነትና በአክቲቪስትነት ስም የተያዙ ሰዎችንም በተመለከተ ‹‹እንኳን በእኛ አገር ቀርቶ በስካንዲኔቪያ አገሮች በሕግ የሚያስጠይቁ ግልጽ የሕግ ጥሰቶችን አንዳንዶቹ መፈጸማቸውን እንደታዘቡ፤›› የሕግ ሙያቸውን በማጣቀስ የሚናገሩት አቶ አንዷለም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ረገድ ያደረጉት ንግግር የተሳሳተ ሆኖ እንዳላገኙት አስረድተዋል፡፡

‹‹ሆኖም አፈና በሚመስልና የሕግ ተጠያቂነት ሒደቶችን ባልተከተለ መንገድ ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ አለመደረጉ ስህተት ነው፤›› የሚሉት አቶ አንዷለም፣ ‹‹ይህን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጥጋቢ መልስ አልሰጡም፤›› ብለዋል፡፡ ተረኝነትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በቀጥታ በቴሌቪዥን ቀርበው ብሔር መቁጠራቸው አስከፍቶኛል፤›› ያሉት አቶ አንዷለም፣ ሕግ ቢወጣ ተብሎ ስለሲቪል ሰርቪሱ የተቀመጠውን ሐሳብም፣ ‹‹እኔ ቢሆን የሚስማማኝ ልክ እንደ ጋና የብሔር ፖለቲካ ከዚህ በኋላ ተከልክሏል ተብሎ ሕግ ቢወጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -