Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ8.7 በመቶ ዕድገት ይመዘገብበታል ተብሎ የነበረው የ2014 ዓ.ም. ኢኮኖሚ ከሰባት በመቶ እንደሚወርድ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የ2015 ዓ.ም. የበጀት ጉድለት 224 ቢሊዮን ብር ወይም 3.4 በመቶ የአገራዊ ምርትን ይይዛል

የ2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ8.7 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ በዓመቱ መጀመሪያ በመንግሥት በኩል ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ይጠበቅ የነበረው አገራዊ ዕድገት ከሰባት በመቶ ሊበልጥ እንደማይችል የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አስታወቁ፡፡

አቶ አህመድ ባለፈው ዓመት ሰኔ 2013 ዓ.ም. የ2014 ዓ.ም. አጠቃላይ በጀት ሲያቀርቡ፣ ኢኮኖሚው በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ ማሻሻያዎችን በተጠናከረ ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግና የግሉን ዘርፍ ዕምቅ አቅም በመጠቀም በ2014 ዓ.ም. የተሻለ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንደሚኖር ገልጸው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ አቶ አህመድ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ከ786 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኖ የቀረበውን የ2015 ዓ.ም. አገራዊ በጀት ሲያቀርቡ በተያዘው ዓመት በነበረው ጦርነት ምክንያት የመንግሥት ገቢ መቀነሱንና ከልማት አጋሮች የሚገኘው የበጀትና የልማት ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በዓመቱ የነበሩ በርካታ መፈናቀሎች፣ የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውድመቶች የመንግሥት ሀብት ለጦርነት በመዋሉ፣ ድርቅ በመከሰቱ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ከታቀደው የ8.7 በመቶ ወርዶ በ6 እና 7 በመቶ መካከል ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የቀጣዩ የ2015 በጀት ዓመት ኢኮኖሚው አሁን ካለበት ችግር በማገገም በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ በተቀመጠው መሠረት የ9.2 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በሌላ በኩል በሚያዚያ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ የታየውን የሸቀጦች ዋጋ 36 በመቶ ማሻቀብ በማስታወስ በ2015 ዓ.ም. መንግሥት አስፈላጊ የፖሊሲና መዋቅራዊ ዕርምጃዎችን ተግባራዊ በማድረግ አማካይ የዋጋ ዕድገቱን ወደ 11 በመቶ ዝቅ ለማድረግ እንደሚሠራ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

ለፓርላማው ከቀረበው አጠቃላይ የ2015 በጀት ውስጥ ለመደበኛ ወጪዎች 345.1 ቢለዮን ብር፣ ለካፒታል ወጭ 218 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 209 ቢሊዮን ብርና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡

ከመደበኛ ወጪ ውስጥ አብዛኛው ገንዘብ ለዕዳ ክፍያ፣ የአገር ደኅንነትን ለማስጠበቅ፣ በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ለሚያስፈልግ የዕለት ዕርዳታ፣ ለአፈር ማዳበሪያና ለስንዴ ግዥ ድጎማ ትልቅ ትኩረት የሰጠ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በሌላ በኩል የካፒታል በጀቱ በመካሄድ ላይ ላሉ ነባር ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ ለማድረግና በጦርነት ምክንያት ለወደሙ መሠረተ ልማቶችንና አገልግሎቶችን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቀቋም ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ አቶ አህመድ አስታውቀዋል፡፡

ለ2015 ዓ.ም. ከቀረበው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 234.4 ቢሊዮን ብር የተጣራ የበጀት ጉደለት እንደሚያጋጥም የተቀመጠ ሲሆን፣ ይህ ጉድለት ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የ3.4 በመቶ ድርሻን ይይዛል፡፡

የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን 224 ቢሊዮን ብር ከአገር ውስጥ ብድርና 6.9 ቢሊዮን ብር ከውጭ አገር የተጣራ ብድር እንደሚወሰድ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለው የበጀት ጉድለቱ ከፍ ሊል የቻለበት ምክንያት አገሪቱ አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር በጣም አንገብጋቢ የወጭ ፍላቶችን መሸፈን የግድ ስለሚል ነው ብለዋል፡፡

የ2015 ዓ.ም. አጠቃላይ የፌዴራል መንግሥቱ ገቢ የውጭ ዕርዳታን ጨምሮ  477 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን፣ ከዚህ ውስጥ 92 በመቶ ከአገር ውስጥ የሚሰበሰብ ሲሆን ከውጭ ምንጭ እንደሚገኝ የሚጠበቀው ደግሞ 38.9 ቢሊዮን በዕርዳታ መልክ መሆኑ ተገልጿ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የካፒታል በጀት ድርሻ እየቀነሰና የመደበኛ በጀት እየጨመረ መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፣ ይህም ለውጥ ሊመጣ የቻለው የመንግሥት የአገር ውስጥና የውጭ ዕዳ  ክፍያ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በቀጣዮቹ ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የፊሲካል ጫናና ሥጋትን የሚያስከትል በመሆኑ፣ የመጪዎቹ ዓመታት የመንግሥት የበጀት ዝግጅት ዋና ትኩረት ከዚህ በፊት በተለይ በጦርነት የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባትና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሁም የዕዳ ክፍያ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ በቀረበው የረቂቅ በጀት መግለጫ ላይ ከመከረ በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ለገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች