Tuesday, May 21, 2024

የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ኢትዮጵያን እስከ 98 ቢሊዮን ብር ለሚደርስ ተጨማሪ ወጪ ይዳርጋታል

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከተጀመረ ወደ አራተኛ ወሩ እያመራ ያለው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት፣ የዓለም የሸቀጦች ዋጋ እንዲንር በማድረጉ፣ ኢትዮጵያ ለምታስገባቸው ሸቀጦች የምትከፍለው ዋጋ ላይ ከ1.52 እስከ 1.9 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ጭማሪ እንድታደርግ እንደሚያስገድድ ተገለጸ፡፡ ይህም አሁን ባለው የዶላር ምንዛሪ ዋጋ ሲሰላ ከ78.73 ቢሊዮን እስከ 98.42 ቢሊዮን ብር ይደርሳል ተብሏል፡፡

መንግሥት ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከሚመጣው የዋጋ ጭማሪ ባሻገር፣ በሁለቱ አገሮች ጦርነት ሳቢያ ወደ ጎረቤት አገሮች የሚደረገው የነዳጅና የስንዴ ኮንትሮባንድ ንግድ ሊጨምር ይችላል የሚል ሥጋት አለው፡፡ 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ግንቦት 29 እና 30 ቀን 2014 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡ በዚህ ግምገማ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈጻጸሞችን የዳሰሰ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ማብራሪያው ላይ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለው አንድምታን አስመልክቶ ያብራሩት ሚኒስትሯ፣ የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት በኢኮኖሚው ላይ የሚሳድረውንም ጫና ዳሰዋል፡፡

እንደ ፍፁም (ዶ/ር) ገለጻ የዋጋ ግሽበት በተለይ ከኮቪድ-19 መከሰት በኋላ፣ ዓለም አቀፋዊ ይዘት በመያዙና የኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትም ከዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ጋር ቁርኝነት ያለው በመሆኑ ተፅዕኖው በግልጽ የሚታይ ሆኗል፡፡ የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መሠረታዊ ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትሯ፣ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ክስተቶች ግን የዋጋ ንረቱን በሚፈለገው ልክ እንዲረጋጋ እንዳላደረጉ አስረድተዋል፡፡

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትም የነዳጅ፣ የምግብና የሌሎች የሸቀጦች ዓለም አቀፋዊ ዋጋ በከፍተኛ መጠን እንዲንር በማድረጉም፣ አገሪቱ በምታስገባቸው ሸቀጦች ላይ ከ1.52 እስከ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ለሚደርስ ለተጨማሪ ወጪ እንደምትዳረግ ተናግረዋል፡፡

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ስንዴ፣ ነዳጅ፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምግብ ዘይት፣ ብረት፣ ጥራጥሬ፣ እንዲሁም ሌሎች ምርቶችን ከሁለቱም አገሮች ታስገባለች፡፡ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከምታስገባው ስንዴ ውስጥ ከሁለቱ አገራት የሚገባው ስንዴ 42 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥም አብዛኛው ከዩክሬን የሚመጣ ነው፡፡ የአገሪቱ 15 በመቶ ብረት፣ ስምንት በመቶ ጥራጥሬና አሥር በመቶ የምግብ ዘይት የሚገባው ከዩክሬን ነው፡፡

ጦርነቱ ተፅዕኖ ካመጣባቸው ምርቶች ውስጥ አንዱ ተብሎ የተጠቀሰው ማዳበሪያ በኮቪድ-19 ምክንያት ከነበረበት በቶን 250 ዶላር ወደ 650 ዶላር ከፍ ብሎ ቢቆይም፣ ጦርነቱ ሲነሳ በቶን ወደ 1,300 ዶላር ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡

ፍፁም (ዶ/ር) በግምገማው ላይ ያነሱት ሌላኛው ሸቀጥ ነዳጅ ሲሆን፣ የአገሪቱን ወርኃዊ የነዳጅ ፍላጎት ለማሟላት ከ395 እከከ 400 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ ቤንዚን በታኅሳስ ወር ከነበረበት በቶን 870 ዶላር በሚያዝያ ወር 1,028 ዶላር ከፍ ብሏል፡፡ ናፍጣ ደግሞ ከነበረበት ከ730 ዶላር በቶን ወደ 1,130 ዶላር ከፍ ማለቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት መንግሥት የነዳጅን ዋጋ ለማረጋጋት ተጨማሪ 120 ቢሊዮን ብር ወጪ ማድረጉንና  85 በመቶውን ጭማሪ ባይሸፍን ኖሮ ቤንዚን በሊትር 73 ብር፣ ናፍጣ ደግሞ በሊትር 67 ብር ይሆን ይሸጥ እንደነበር አክለዋል፡፡

የማዳበሪያ ዋጋም ከኮቪድ በፊት በቶን 250 የአሜሪካ ዶላር የነበረው በኮቪድ ምክንያት በቶን ወደ 650 የአሜሪካ ዶላር ካደገ በኋላ፣ ጦርነቱ ሲጀመር በቶን ወደ 1,300 ዶላር መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ሩሲያና ዩክሬን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው የዘይት አቅርቦት ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠረው ተፅዕኖ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱም ተገልጿል፡፡ ከዩክሬን ይመጣ የነበረው ዘይት ከመቋረጡም ባሻገር 41 በመቶው ዘይት የሚገዛባት ማሌዥያ በጦርነቱ ምክንያት ለአገር ውስጥ ገበያ ቅድሚያ በመስጠቷ፣ ቀጥተኛ ያልሆነ ተፅዕኖም ኢትዮጵያ ላይ ማረፉ ተጠቅሷል፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች ሲደመሩም ጦርነቱ አገሪቷን እስከ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ለሚደርሰው ተጨማሪ ወጪ እንደሚዳርጋት ፍፁም (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

በተከታታይ እየተከሰተ ያለው ይህ የዋጋ ንረትም በሚፈጥረው ኢተገማች ያልሆነ ሁኔታ የተነሳ ኢንቨስተሮች ምርታማ ከሆኑና ዘላቂ የሥራ ዕድል ከሚፈጥሩ ዘርፎች ይልቅ፣ እንደ ቤትና መኪና ያሉ ንብረቶች ላይ ኢንቨስት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትም ቢሆን ካለው ኢተገማች ሁኔታ ጋር ተያይዞ የኢንቨስትመንት ውሳኔ ሊዘገይ እንደሚችልም ሥጋታቸውን አክለዋል፡፡

ዘጠና በመቶ የሚሆነው የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ስንዴ የሚመጣው ከሩሲያና ከዩክሬን ለመሆኑ፣ ይህም በጦርነቱ ሳቢያ መስተጓጎሉ ስንዴ ከኢትዮጵያ በሕገወጥ መንገድ ሊወጣ ይችላል የሚል ሥጋት ተፈጥሯል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ መጨመሩና ኢትዮጵያም ነዳጅን በድጎማ ባነሰ ዋጋ የምትሸጥ መሆኗን፣ አሁንም ያለውን የነዳጅ ኮንትሮባንድ ሊያንረው እንደሚችል የተናገሩት ፍፁም (ዶ/ር)፣ ‹‹ሕገወጥ ነዳጅን መልሶ ወደ ጎረቤት አገሮች ኤክስፖርት ሁኔታ ሊባባስ ይችላል፣ ለዚህም ትልቅ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -