Saturday, May 18, 2024

ቻይና የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጉባዔ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ማቀዷ ተሰማ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቻይና በሰኔ ወር መጨረሻ አካባቢ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጉባዔ ለማካሄድ ቀጠሮ መያዟን፣ በቻይና ታዋቂ የሆነው ሳውዝ ቻይና ፖስት ማክሰኞ ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ዘገባ አስታወቀ፡፡

በዘገባው መሠረት በሱዳን የቻይና አምባሳደር ማ ዢንሚን ለሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጠባባቂ ምክትል ዋና ጸሐፊ ናዲር የሱፍ አል ጠይብ እንደነገሩት፣ ቻይና በጣም አስፈላጊ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ የሰላም ጉባዔው እንዲደረግ ተነሳሽነቱን የወሰደችው መረጋጋት፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን ነው፡፡

በእርስ በርስ ጦርነት፣ በታጣቂዎች ጥቃት፣ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥትና በከፋ ድህነት ቁም ስቅሉን በሚያየው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሱዳን፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሶማሊያ መኖራቸውን የጠቀሰው ዘገባው፣ ቻይና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ጉባዔውን ለማዘጋጀት መወሰኗን አትቷል፡፡

ቻይና ከዚህ ቀደም ትከተል የነበረውን በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለ መግባት ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ፣ አሜሪካ በአገሮች የውስጥ ጉዳይ መፈትፈቷን እንድታቆም ስትወተውት ትታወቃለች፡፡ አገሮች የራሳቸውን ውስጣዊ ችግሮች በራሳቸው እንዲፈቱም ታበረታታ ነበር፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢኮኖሚዋ ፈርጣማ የሆነችው ቻይና በተለይ በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለው የሰላም ዕጦት ለጥቅሟ ተፃራሪ ስለሚሆን፣ ይህንን የሰላም ጉባዔ ለማዘጋጀት ሊያስገድዳት እንደቻለ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች መናገራቸው ተዘግቧል፡፡

ይህንንም ሐሳባቸውን ሲያጠናክሩ ቻይና በአፍሪካ ቀንድ አገሮች ውስጥ ከምትሳተፍባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተጨማሪ፣ በትሪሊዮን ዶላር የሚገመተው ለወደቦች፣ ለአውራ መንገዶች፣ ለግድቦችና ለባቡር መስመሮች ግንባታ የሚያገለግለው የቻይና ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ መላውን አፍሪካ ለማስተሳሰር ስለሚጠቅማት ጉባዔውን ለማካሄድ ምክንያት እንደሚሆናት አስረድተዋል፡፡

በጃፓን ዶሺሻ ዩኒቨርሲቲ የግሎባል ስተዲስ ፕሮፌሰር ሰይፈዲን አደም ለሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት እንደተናገሩት፣ ቻይና በዚህ ውሳኔዋ ‹‹ወደ የማይታወቅ ሥፍራ›› በመግባት የአካባቢውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ገንቢ የሆነ ሚና ልትጫወት ትችላለች፡፡

‹‹ቻይና በሁለት አቀራረቦች መሀል ያለውን ፉክክር ልታሳይ ብሥራት ይዛ መጥታለች፡፡ የመጀመርያው የምዕራባውያን መንገድ እስካሁን ብዙ ተሞክሮ አልሠራም፣ አሁን ደግሞ የእስያውያን መንገድ በአፍሪካ ቀንድ ሊሞከር ቀርቧል፤›› ብለዋል፡፡

ቻይና በቅርቡ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ በማድረግ የሰየመቻቸው ዡዪ ቢንግ በመጋቢት ወር በኬንያ፣ በኤርትራ፣ በኡጋንዳ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በጂቡቲና በሶማሊያ ጉብኝት በማድረግ ከአገሮቹ መሪዎች ጋር ተገናኝተው መምከራቸው ለሰላም ጉባዔው ዝግጅት እንደሆነ በዘገባው ተካቷል፡፡

በኢትዮጵያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደርና በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ኢሊየት ስኩል ኦፍ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ሺን፣ በቻይና አስተባባሪነት ይካሄዳል ከተባለው የሰላም ጉባዔ ብዙ እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡

‹‹ችግሮቹ ብዙና ውስብስብ ናቸው፤›› የሚሉት ሺን፣ ተቀናቃኞቹ ግን የሚያሳዩነት ፈቃደኝነት አናሳ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ቻይና ጥሩ አዳማጭ ናት፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል ጠንከር ያሉ ጠንካራ ዕርምጃ ለሚያስፈልጋቸው የግጭት አፈታት ጉዳዮች ያሳየችው ፍላጎት አናሳ ነው፤›› በማለት ያክላሉ፡፡

እሳቸው እንዲህ ቢሉም ቻይና የዚህ ጉባዔ መካሄድ ጠቀሜታው ከመቼውም ጊዜ ስለሚያስፈልጋት፣ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይን በልዩ ሁኔታ መያዟን ነው ለዘገባው አስተያየታቸውን የገለጹ ባለሙያዎች የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -