Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበአበርገሌ ወረዳ የተከሰተውና ስምንት ሰዎችን ገድሏል ለተባለው ወረርሽኝ ምላሽ የሚሰጥ አካል አልተገኘም

በአበርገሌ ወረዳ የተከሰተውና ስምንት ሰዎችን ገድሏል ለተባለው ወረርሽኝ ምላሽ የሚሰጥ አካል አልተገኘም

ቀን:

ከግንቦት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ሪፖርት የተደረገውና በአማራ ክልል በዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አበርገሌ ወረዳ ተከሰተ ለተባለው ወረርሽኝ፣ ምላሽ ለመስጠት የሄደ አካል አለመኖሩ ተነገረ፡፡ የዞኑ ጤና መምርያ የችግሩን ምንነት ለማወቅ በርካታ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሄደው የተመለሱ ቢሆንም፣ ነገር ግን ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት ያደረገ የለም ብሏል፡፡ ተቋማቱ በርቀት መረጃ ሰብስበው ከመመለስ ባለፈ፣ ችግሩ ወደ ደረሰበት አበርገሌ አለመንቀሳቀሳቸው ተመልክቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አካላት፣ ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማትና ኤጀንሲዎች የወረርሽኙ ሪፖርት እንደ ደረሳቸው፣ ከጤና ሚኒስቴር ቡድን ጋር ወደ ሰቆጣ ሄደው ነበር ተብሏል፡፡ ወረርሽኙ ተከሰተ የተባለበት አበርገሌ ወረዳ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር የሚገኝ በመሆኑ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማቱ ምላሽ እንዲሰጡ ተጠይቀው እንደነበር ተገልጿል፡፡

ተቋማቱ ጥያቄውን ቢስማሙበትም ነገር ግን ስለሁኔታው በርቀት ሰምተው ከመሄድ ባለፈ፣ ለተጨማሪ ማጣራትም ሆነ ምላሽ ለመስጠት አለመመለሳቸውን የዞኑ ጤና መምርያ ኃላፊ ዶ/ር ኪዳት አየለ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ስለወረርሽኙ ምንነትና ስለደረሰው ጉዳት የተጠየቁት ዶ/ር ኪዳት፣ ‹‹ሦስት ሕፃናት የዕብድ ውሻ በሽታ ዓይነት ምልክት ባለው ሕመም መሞታቸውን፣ እንዲሁም አምስት ተጨማሪ ሰዎች የተለየ ምልክት ባለው ሕመም መሞታቸው ሪፖርት ተደርጎልናል፤›› ብለዋል፡፡

ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ማስመለስና የአፍ መድረቅ የሕመም ምልክቶች የሚታይባቸው በጥቅሉ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን ሪፖርት መደረጉን የዞኑ የጤና መምርያ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በተጨማሪ የሕክምና ምርመራ እስካልተረጋገጠ ድረስ ሕመሙን፣ ‹‹የዕብድ ውሻ በሽታ ወይም ሌላ ዓይነት ወረርሽኝ ነው ብለን ልንደመድም አንችልም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ወረርሽኝ ተከሰተበት የተባለው የአበርገሌ አካባቢ በወባ የሚጠቃ መሆኑን አስታውሰው፣ አካባቢው ለረጅም ጊዜ በሕወሓት ቁጥጥር ሥር በመሆኑ ክትባትም ሆነ ሌላ የሕክምና አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የምግብ እጥረትና መሠረታዊ የሕክምና አገልግሎት አቅርቦት እጥረት ስላለ፣ በአካባቢው ማንኛውም ዓይነት ወረርሽኝ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑን ዶ/ር ኪዳት ጠቁመዋል፡፡

የክልሉ ጤና ቢሮ፣ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴርና በጤና ላይ የሚሠሩ አጋር አካላት በወረዳው የወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ክፍል አማካይነት ሪፖርት ተደርጎላቸዋል ተብሏል፡፡ ወደ አካባቢ በመሄድ ሁኔታውን ለመገምገምም ሆነ ምላሽ ለመስጠት፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት የቀለለ እንደነበር ዶ/ር ኪዳት ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ጉዳዩን ሰምተው ‹‹እንመጣለን›› በሚል ቃል የተመለሱት ተቋማቱ በዛው የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል ብለዋል፡፡

ወረርሽኝ ተብሎ በአበርገሌ ካሉ ሰዎች ሪፖርት የተደረገውና ስምንት ሰዎች መግደሉ የታወቀው ሕመም፣ አሁን ስለሚገኝበት ሁኔታና ስላደረሰው ተጨማሪ ጉዳት የሚታወቅ መረጃ እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ