Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሞያሌና በቶጎ ጫሌ ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴ በመጨመሩ ባንኮች ዕገዳ ተጣለባቸው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የውጭ ምንዛሪና የብድር አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል

በሞያሌና ቶጎ ጫሌ ከተሞች የሚገኙ ባንኮች ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ እንቅስቃሴቸው በመጨመሩ ዕገዳ ተጣለባቸው፡፡

 በሁለቱ አካባቢዎች የሚገኙ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን ወደ ንዑስ ቅርንጫፍ ዝቅ አድርገው እንዲሠሩ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪና ብድር አገልግሎት እንዳይሰጡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በደብዳቤ አግዷቸዋል፡፡

ሪፖርተር ያገኘውና ብሔራዊ ባንክ በቶጎ ጫሌና በሞያሌ ለሚንቀሳቀሱ የባንክ ቅርንጫፎች የላከው ደብዳቤ እንደሚያመላክተው፣ ሁሉም ባንኮች ውሳኔውን ከግንቦት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋሉ፡፡

በ2000 ዓ.ም. የተሻሻለውን የባንክ ሥራ አዋጅ በመጥቀስ ብሔራዊ ባንክ በቶጎ ጫሌና በሞያሌ የባንኮችን አሠራር አስመልክቶ አካሄድኩት ባለው ፍተሻና ምርመራ መሠረት፣ ባንኮቹ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የፋይናንስ ፍላጎት መሠረት ከማድረግ ይልቅ በሕገወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ላይ ተሰማርተው እንዳገኛቸው አስታውቋል፡፡

በዚህ መሠረት ባንኮች በተፈቀዱላቸው ንዑስ ቅርንጫፎች ውስጥ በተገደበ አሠራር ገንዘብ ገቢና ወጪ እንዲያደርጉ፣ በእነዚህ ንዑስ ቅርንጫፎች ብቻ ለአካባቢው ነዋሪዎችና በመረጃ በመደገፍ ለታወቁ ድንበኞች አገልግሎት እንዲሰጡ ብሔራዊ ባንክ አሳስቧል፡፡

በተጨማሪም በቶጎ ጫሌና በሞያሌ በተከፈቱ የባንክ ሒሳቦች ገቢ የሚደረግ፣ ወይም ወደ እነዚህ ንዑስ ቅርንጫፎች የሚላክ ገንዘብ ላይ ገደብ ተጥሏል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች በጻፈው ደብዳቤ ሁሉም ባንኮች ትዕዛዙን እንዲፈጽሙ በጥብቅ ያስታወቀ ሲሆን፣ አፈጻጸማቸውን ሪፖርት እንዲደርጉ አሳስቧል፡፡

በሞያሌና በቶጎ ጫሌ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች እየሠሩባቸው ያሉ የቅርንጫፍ ፈቃዶችን በመመለስ፣ የንዑስ ቅርንጫፍ ፈቃድ እንዲወሰዱ ብሔራዊ ባንክ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

በብሔራዊ ባንክ ውስጥ ከፍተኛ አመራር የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በቶጎ ጫሌ ብቻ 15 ባንኮች 19 ቅርንጫፎች ከፍተው ይንቀሳቀሳሉ፡፡

እነዚህ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን ወደ ንዑስ ቅርንጫፍ ዝቅ ሲያደርጉ ብድር መስጠት እንደማይችሉና በውጭ ምንዛሪ ሥራ እንደማይሰማሩ የገለጹት ኃላፊው፣ ዋነኛ ሥራቸው ቁጠባ ይሆናል ብለዋል፡፡

ለባንኮች በተላለፈው ደብዳቤ መሠረት አንድ ግለሰብ ሞያሌ ወይም ቶጎ ጫሌ ቢሄድ፣ በሁለቱ አካባቢዎች ቅርንጫፎች ሌላ ቦታ ከከፈተው የባንክ ሒሳቡ ገንዘብ ማውጣት አይችልም፡፡

ይህ አሠራር በተለይ በመሀል አገር ወይም በሌሎች አካባቢዎች በከፈተ የባንክ ሒሳብ፣ ወደ እነዚህ የድንበር አካባቢዎች ተጉዞ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚፈልግ ሕገወጥ ሰው ለመቆጣጠር መሆኑን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክን ውሳኔ በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፣ በተጠቀሱት አካባቢዎች ጥሩ የሚባል የባንክ እንቅስቃሴ አለመኖሩንና ባንካቸው ለበለጠ ወጪ እንደሚዳረግ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ውሳኔው በዳሸን ባንክም ሆነ በሌሎች ባንኮች ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች