Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹አትሌቲክስ ማጭበርበሮች የበዙበትና ፖለቲካ የገባበት ስፖርት ሆኗል›› አቶ ቢንያም ምሩፅ ይፍጠር፣ የአዲስ...

‹‹አትሌቲክስ ማጭበርበሮች የበዙበትና ፖለቲካ የገባበት ስፖርት ሆኗል›› አቶ ቢንያም ምሩፅ ይፍጠር፣ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፈዴሬሽን ፕሬዚዳንት

ቀን:

2012 .ም. ለአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለፕሬዚዳንት ዕጩ ሆነው ሲቀርቡ፣ በአትሌቲክሱ ላይ የራሳቸውን አሻራ እንዲሁም የአባታቸውን የኦሊምፒክ ጀግና ምሩፅ ይፍጠርን ውርስ (ሌጋሲ) ለማስቀጠል ነበር መነሻ የሆናቸው። የአመራርነት ቦታውን ከተረከቡ በኋላ የጠበቁትን እንዳላገኙ ይልቁንም የተገላቢጦሽ መሆኑን ያስታውሳሉ። ይኼም ፌዴሬሽኑን ሰንቅረው የያዙ በርካታ ችግሮች ከመኖራቸውም በላይ፣ ፌዴሬሽኑ የረባ ቢሮ እንኳን የሌለው መሆኑን ተከትሎ እንደ አዲስ መለወጥ ግድ ይል ነበር። ቀድሞ ጃንሜዳ የነበረው የፌዴሬሽኑ ቢሮ፣ የተጎሳቆለና አትሌቲክሱን የማይመጥን መሆኑን ተከትሎ፣ የአዲስ ተመራጩ ሥራ አስፈጻሚን ዳግም ማደራጀት ቀዳሚ ሥራ ነበር።  ከዚህም ባሻገር ብቁ ባለሙያዎች የሌሉትን የአገሪቷ ዋና ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አዲስ ባለሙያዎችን ቀጥሮና 800 ሺሕ ብር በላይ ወጪ በማውጣት፣ አዲስ ወደ ተከራየው ቢሮ ገብቶ እንደ አዲስ ማደራጀቱን ተያይዘውታል። በዚህም መሠረት ዘመናዊ መንገድ የተከተለና ሥራን ሊያቀላጥፍ በሚችል መልኩ የተደራጀው ፌዴሬሽኑን፣ ለተለያዩ የክልል ፌዴሬሽኖች ምሳሌ መሆን የቻለ የቢሮ አደረጃጀት ማዋቀር መቻላቸውን ይገልጻሉ። ስለአዲስ አበባ አትሌቲክስ እንቅስቃሴና ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ቢንያም ምሩፅን ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ አዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራርነት ከመጣችሁ በኋላ ምን ያሻሻላችሁት ነገር አለ?

አቶ ቢንያም፡- ኃላፊነት ከተረከብን በኋላ ቢሮውን እንደ አዲስ ከማደራጀት፣ አዳዲስ ባለሙያዎችን ከመቅጠር ባሸገር፣ አዲስ ዌብሳይት በመፍጠር እስከ ዛሬ በፌዴሬሽኑ የተከናወኑ ተግባራት በአንድ ቋት ውስጥ እንዲቀመጡና በቀላሉ እንዲገኙ የሚያስችል መንገድ ፈጥረናል። ከዚያም ባሻገር እያንዳንዱ ክለብ ስንት አትሌት እንዳለው፣ አሠልጣኞቹ እነማን እንደሆኑ፣ እስከ ዛሬ ክብረ ወሰኖች በማንና መቼ እንደተያዙ መረጃን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል የመረጃ ቋት አስረድተናል። ከዚህ በኋላ ማንኛውም አትሌት መመዝገብ ሲፈልግ ካለበት ሥፍራ ሆኖ መመዝገብ የሚችልበትና ማንኛውም መረጃ ከዌብሳይቱ ማግኘት እንዲያስችል አቀናጅተናል። ሌለው ከዚህ ቀደም ሥልጠና ውድድር ተኮር የነበረ ሲሆን፣ የታዳጊ ፕሮጀክቶች በትምህርት ቤት መኖር አለበት በማለት የሕፃናት አትሌቲክስን በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ ዕድሜያቸው ከ8 እስከ 13 ዓመት ባሉ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን አስጀምረናል።

- Advertisement -

በ2015 ዓ.ም. ደግሞ ሁሉም ክለቦች ታዳጊዎችን መያዝ አለባቸው በሚል ሐሳብ ላይ ተወያይተናል። በዚህም ታዳጊ መያዝ ካልቻሉ እንደ ክለብ መቀጠል እንደማይችሉ አቋም ይዘናል። በተጨማሪ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ፌዴሬሽን እንዲቋቋም በማድረግ፣ በቀጣይ ዓመት በጀት ኖሯቸው ክለብ የሚይዙበትና ውድድር ላይ የሚሳተፉበት መንገድ አመቻችተናል።

ሪፖርተር፡- ዓመታዊ ውድድሮችን ማሳደጉና ማስፋፋቱ ምን ይመስላል?

አቶ ቢንያም፡- በዓመት ከአሥር ያላነሱ የተለያዩ ውድድሮች እናደርጋለን፡፡ ምንም እንኳ በቂ ናቸው ባይባልም፡፡ የአዲስ አበባ ሻምፒዮና፣ አገር አቋራጭ፣ ማራቶን፣ ግማሽ ማራቶን፣ የክፍለ ከተሞችና የታዳጊዎችን ጨምሮ በርካታ ውድድሮችን እናከናውናለን፡፡ የውድድር ዕጥረት መኖሩን ተከትሎ ዘንድሮ ተጨማሪ የአጭር ርቀት ውድድሮችን ለመጨመር አቅድናል፡፡ የውድድር ቁጥርን ለመጨመር ግን ተጨማሪ በጀት ያስፈልጋል፡፡ እኛ እነዚህንም ውድድሮች ለማከናወን ምንም ዓይነት በጀት የለንም፡፡ በስፖንሰር ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ ያንን በማብቃቃት የክለቦቻችንን የውድድር ፍላጎት ለማሟላት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ጋር በመወያየት የትምህርት ቤት ውድድሮችን ለማስጀመር በሒደት ላይ ነን፡፡ ስፖርቱን ለማሳደግ የትምህርት ቤት ውድድሮችን ማከናወን ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወቅታዊው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ቢንያም፡- ሥጋት አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአግባቡ ስፖርቱን እየመራው ነው ለማለት ይቸግረኛል፡፡ ምክንያቱም ትናንት 1,500 ሜትር ርቀት ላይ የሚሮጥ አትሌት፣ ቀጥታ ወደ ማራቶን ሲገባ እየተመለከትን ነው፡፡ ይኼንን የሚመራው የበላይ አካል ሆኖ ፌዴሬሽኑ ቢሆንም በአግባቡ መምራትና መቆጣጠር ግን አልቻለም፡፡ ማናጀሮችን ምን ያህል ይቆጣጠራል የሚለው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡  ፌዴሬሽኑ ከክለቦች ጋር ያለው ግንኙነት ጤናማ አይደለም፡፡ ከዚህም ባሻገር በአትሌቲክሱ የሚሠሩ ሕገወጥ ተግባሮች አሉ፡፡ በተጭበረበረ መንገድ ወደ ላይ ለመውጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ አለ፡፡ እሱን በአግባቡ መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ራሱን መመልከትና ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል የሚስተዋሉ አተካሮዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል  በዚህ ሳምንት በጀመረው የመጀመሪያው የአትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ አከራካሪ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

አቶ ቢንያም፡- ከ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ጀምሮ በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚነሳው ጉዳይ በጣም አወዛጋቢ እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ አንዴ ሰላም ፈጥረዋል ሲባል፣ በሌላ ጊዜ አከራካሪ ጉዳዮች ሲነሱ መመልከት እየተለመደ መጥቷል፡፡ በሐዋሳ እየተከናወነ የሚገኘውን የመጀመሪያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ቅድመ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እስከመጨረሻው ቀን ድረስ የጨዋታው አካል እንደሆነ ነበር የምናውቀው፡፡ ምክንያቱም ለጨዋታው አውራ ደንብ ሲወጣ ፌዴሬሽኑ ሊኖረው የሚችለውን ድርሻና ተሳትፎ አንዱ አካል ነበርና፡፡ ሆኖም ውድድር ሊጀመር አንድ ቀን ሲቀረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአቋም መግለጫ ይዞ ወጣ፡፡ ይኼ አንድ ትልቅ ተቋም ከሚመራ ፌዴሬሽን የሚጠበቅ አይደለም፡፡

በእርግጥ ብሔራዊ ፌዴሬሽን የነበረው አቋም ውድድሮች በብሔራዊ ፌዴሬሽኖች መመራት አለባቸው የሚል ነው፡፡ ጥያቄው ትክክልና አግባብ ቢሆንም የጠየቀበት ጊዜ የውድድር መዳረሻ ላይ ማድረጉ ግን ፍፁም ስህተት ነው፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መምራት ያለበትን ውድድር 90 በመቶ እኔው ካልመራሁ ያለበት መንገድ ትክክል አይደለም፡፡ ትንሽ አምባገነንነት ይታይበታል፡፡ በሁለቱ ተቋማት ምክንያት ዳኞች፣ አሠልጣኖች፣ አትሌቶች እንዲሁም አመራሮች ሳይቀሩ ለሁለት የተከፈሉበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ በእውነቱ እኔ በግሌ አንገት የደፋሁበት ጊዜ ይኼ ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምን ዓይነት አቋም ነበረው?

አቶ ቢኒያም፡- እንዲዚህ ዓይነት ሽኩቻ መኖሩ ተገቢ አይደለም፡፡ እኛ የተንቀሳቀስነው የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ወክለን ሳይሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ያሉትን ተወዳዳሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ በጨዋታው ላይ የመካፈል ሆነ ያለመካፈል ውሳኔ የከተማ አስተዳደሩ ስለሆነ፣ በጨዋታው እየተሳተፍን እንገኛለን፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ግን በዚያ መንገድ የተገነዘበው አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የነበረውን አቋም ያውቅ ነበር?

አቶ ቢንያም፡- እኛ እስከ መጨረሻ ድረስ የምናውቀው ነገር አልነበርም፡፡ በሁለቱ ተቋማት መካከል የሚከሰተው አለመግባበት ሰው የቱ ጋ መቆም እንዳለበት እንኳን የሚቸገርበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ስፖርቱን እየገደለው ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ስፖርቱን ብቻ መመልከት ተገቢ ነው፡፡ አንደኛው ቡድን ወደ ግራ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ወደ ቀኝ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ይኼ ደግሞ ስፖርቱን አይጠቅምም፡፡ በዚህ ውድድር ላይ ለመካፈል የመጡ ተሳታፊዎች ጨዋታው ይደረጋል አይደረግም ብለው ግራ መጋባት የለባቸውም ነበር፡፡ ሁሌም ቅድሚያ ለስፖርቱ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ሌላውን ሽኩቻ ሌላ ቦታ ቢጨርሱትና ጨዋታው ላይ ብቻ ቢያተኩሩ ይሻላል፡፡ በዚህም ጨዋታ ተመሳሳይ ነገር ተንፀባርቋል፡፡ ይኼን የሚፈታው አካል ሊፈታው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡-  የአዲስ አበባ ስታዲየም በግንባታ ላይ በመሆኑ በርካታ በተለይ የመም አትሌቶች በልምምድ ሥፍራ ዕጦት ተመተዋል፡፡ ይኼን ችግር ለመፍታት ምን እየተደረገ ነው?

አቶ ቢንያም፡- በአዲስ አበባ ያሉት ክለቦች ንግድ ባንክ፣ መከላከያ፣ ኤሌክትሪክ፣ ማረሚያና ፌደራል ፖሊስን ጨምሮ የልምምድ ቦታ በማጣታቸው፣ ሱሉልታ በሚገኘው የቀነኒሳ ትራክ ላይ በአትሌት በቀን ከ150 ብር እስከ 200 ብር እየከፈሉ ልምምድ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ከአትሌቲክሱ የሚጠበቀው ውጤት እና የሚሰጠው ድጋፍ አነስተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ውድድር ለማድረግ አንድም ቦታ የለም፡፡ ወጣቶች አካዴሚም ዕድሳት ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ስታዲየም ከተዘጋ ቆይቷል፡፡ በአበበ ቢቂላ 25 ተጨዋች በሜዳው አንድ ጊዜ የእግር ኳስ ልምምድ ለማድረግ 1,500 ብር ነው የሚጠየቀው፡፡ በአንፃሩ ለአንድ አትሌት 200 ብር ነው የሚጠየቀው፡፡ ለእግር ኳስና ለአትሌቲክስ እንኳን የሚሰጠው ትኩረት እኩል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- ችግሩን ለመፍታት ያደረጋችሁት ጥረት አለ?

አቶ ቢንያም፡- ለከተማ አስተዳደሩ ቸግሩ እንዲፈታ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ ለዚያም ይረዳን ዘንድ በአንደኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የምናደርገው ተሳትፎና ውጤት ችግሩን በአፋጣኝ እንዲፈታልን የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡ ከዚያ ባሻገር በከተማዋ ባሉ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በርካታ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች አሉ፡፡ ግን ዝግ ሆነው ነው የሚውሉት፡፡ እነዚህ ለአትሌቱ ክፍት ሊሆኑ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀጣይ ዕቅድ ምንድነው?

አቶ ቢንያም፡- በእውነቱ ከሆነ አዲስ አበባ ላይ ለአትሌቲክሱ የተሰጠው ትኩረት በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ይኼንን ለመቀየር ውጤት ማምጣት ግድ ይላል፡፡ ውጤት በማምጣት ጥያቄም ለመጠየቅም ያስችላል፡፡ ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከከንቲባ ቢሮ እንዲሁም ከከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የሚሰጠን አንድም በጀት የለም፡፡ በቀጣይ ክለቦች እንዲሁም ፕሮጀክቶች ላይ ለመሥራት ላሰብነው ሥራ በጀት ያስፈልገናል፡፡ አዲስ አበባን የሚወክል አንድ የአትሌቲክስ ቡድን እንፈልጋለን፡፡ ያንን ለማዋቀር በጀት ያስፈልጋል፡፡ ነገ ከተማ አስተዳደሩን የሚወክሉ አትሌቶችን ማፍራት ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- በመጨረሻም የሞስኮ ኦሊምፒክ  ባለድሉ ምሩፅ ይፍጠር ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› ልጅ ነህ፡፡ ወደ አትሌቲክሱም የገባኸው የእሱን ውርስ ለማስቀጠል በሚል መነሻ ሐሳብ ነው፡፡ ተሳክቶልኛል ብለህ ታስባለህ? ከዚያም ባሻገር ከአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራርነት ወደ ኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  አመራርነት የመምጣት ትልም አለህ?

አቶ ቢንያም፡- ወደ አትሌቲክስ አመራርነት ከመምጣቴ በፊት የነበረኝ ግምትና ውስጡ ስገባ በጣም የተለያየ ነው፡፡ በአትሌቲክስ ውስጥ በጣም አስቸጋሪና ውስብስብ ነገሮች አሉበት፡፡ ፖለቲካ የገባበትና ብዙ ተንኮልና ሸፍጥ ያለበት ስፖርት ነው፡፡ በዚህም በጣም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ በኋላ በስፖርቱ እቀጥላለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ግን ባለፉት ሦስት ዓመታት ከሌሎች የሥራ አስፈጻሚዎች ጋር ሆኜ የተሻለ ነገር ሠርተናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአባቴ ስም ዓመታዊ ውድድር ለማድረግ ዕቅድ ነበረኝ፡፡ ግን አሁን ያለሁበት ሁኔታ ያንን ለማድረግ አይፈቅድም፡፡ ግን የእሱን ስም የሚዘክሩ ውድድሮችና አንዳንድ ሥራዎች ለመሥራት እየተንቀሳቀስኩ ነበር፡፡ ወደ ፊት የማይቀር ነው፡፡ አባቴ ለኢትዮጵያ ያበረከተውን ያህል ኢትዮጵያ አልከፈለችውም፡፡ እኔም ወደ አትሌቲክሱ የመጣሁት የእሱን እግር በመከተል ነበር፡፡ በስሙ አንድም አደባባይ፣ መንገድ አለመሰየሙና በስሙ ማዕከል እንኳን አለመቋቋሙ ያሳዝናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...